አምራች ኢንዱስትሪዉን ለማሳደግ ከአጋር አካለት ጋር የሚደረገው የቅንጅት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል( አቶ ሀሰን መሐመድ)

የአምራች ኢንዱስትሪውን በማዘመን በዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን የሚደረገዉን ጉዞ ለማስቀጠል ከአጋር አከላት ጋር ተናቦና በትብብር መንፈስ መስራት ትኩረት የተሰጠው ተግባር መሆኑ ተገልጿል ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በአምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ያጋጠመ ያለውን የሃይል መቆራረጥ ፤ የሰብስቴሽን ግንባታ መዘግየት፣የግምት እና ክፍያ መዘግየት፣የተለያዩ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ መዘግየት እና ሌሎች ችግሮች አስመልክቶ ከኢትዮጵያ አሌክትሪክ ሃይል እና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አመራሮች፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች እና ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱ ወቅት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የመሰረተ ልማት ግብዓት ዘርፍ ሚኒስተር ዴኤታ አቶ ሃሰን መሃመድ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ፣ለስራ ፈጠራ፣ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ያሐው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ዘርፉ ያለ ዘለቂና በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የተፈለገዉን እድገት ማረጋገጥ ስለማይችል የተፈጠሩ ችግሮችን እንደየ አስፈላጊነታቸው የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ በተቀናጀ መንገድ መፍታት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ሀሰን የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦትን ማሻሻል የአምራች ኢንዱስትሪዉን የስራ ስኬት ለማጠናከር፣ የሀገራችንን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እና የህዝባችንን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ በግልጽነት እና በተጠያቂነት ሀላፊነትን መወጣት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም ከአምራች ኢንዱስተሪ ባለቤቶችና ተወካዮች ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ተነስተው በተቋማቱ አመራሮች ምላሽ እና ማብራሪያዎች ተሰጥተዋል፡፡

Share this Post