የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ የምግብ ማበልፀግ ፕሮግራም ትግበራ አፈፃፀም ሪፖርት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች ለተቋቋመው ኮሚቴ አቀረቡ ፡፡

ጥር 21/2018 ዓ.ም (ኢሚ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በሪፖርቱ እንደገለፁት የምግብ ማበልፀግ ፕሮግራም ያለበት ደረጃ እና በአተገባበር ጊዜ ያጋጠሙ ችግሮች እንዲሁም የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎችን በቀጣይ ያለውን የትኩረት አቅጣጫ በዝርዝር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች ለተቋቋመው ኮሚቴ አብራርተዋል ፡፡

እንደ ሀገር በተጀመረዉ ብሔራዊ የምግብ ማበልፀግ ፕሮግራም በአስገዳጅነት ፋብካሪዎች የምግብ ዘይት፣ ስንዴ ዱቄትና የጨው ምርት በቫይታሚንና ማዕድን የበለፀጉ እንዲሆኑ በማድረግ የሚታይ ለዉጦች ማምጣት ተችሏል ሲሉ ገልፀዋል ፡፡

አያይዘዉም በሀገር ዉስጥ የሚመረቱትን ብቻ ሳይሆን ወደ ሀገር ዉስጥ የሚገቡ የምግብ ምርቶችም የሚፈቀዱት በቫይታሚንና በማዕድን የበለፀጉ መሆናቸዉ ሲረጋገጥ እንደሆነ ገልፀው ምግብን ማበልፀግ የአመጋገብ ጥራትን ለማሻሻልና ለጤና ጠቃሚ እንዲሆን ተጨማሪ አልሚ ንጥረ-ነገሮችን በመጨመር የተመጣጠነ የምግብ እጥረትን መከላከልን አላማው ያደረገ አስገዳጅ ህግ አውጥተን እየሰራን እንገኛለን ሲሉ ገልፀዋል ፡፡

አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ 130 ኢንዱስትሪዎች ምግብን በንጥረ ነገሮች አበልጽጎ ወደ ማምረት የገቡ መሆናቸውን ተናግረዎል።

ቀጥለውም ሚኒስቴር ዴኤታው እንደገለፁት የምግብና ሥርዓተ ምግብ ስትራቴጂ መነሻ ዳሰሳ ጥናት እንደሚያመለክተው የሕፃናት መቀንጨር አሁንም የኢትዮጵያ ዋና የህብረተሰብ ጤና ችግር ሆኖ ቀጥሏል ሲሉ ገልፀው የቫይታሚንና ማዕድናት እጥረትን ለመቀረፍ የሚረዱ መፍትሄዎች የምግብ ስብጥር፣ በተሟላ ንጥረ-ነገር ፣ ምግብን ማበልፀግ እና የሰብል ዝርያ ማሻሻል መሆናቸውን ገልፀዋል ፡፡

የብሔራዊ ምግብ ማበልጸግ ስትሪንግ ኮሚቴና ቴክኒካል ኮሚቴ በየሩብ ዓመቱ የምግብ ማበልጸግ ያስተባብራል፣ ትግበራ ሂደቱን ይገመግማል፣ የትግበራ አቅጣጫ ይሰጣል ሲሉ ገልፀው ለፌደራል እና ለክልልና ከተማ መስተዳድር ባለድርሻ አካላት አቅም ግንባታ ስልጠኛዎች ተሰጥቷል ሲሉ ገልፀዋል ፡፡

በተጨማሪም ለስንዴ ዱቄትና ዘይት አምራቾች ስለምግብ ማበልፀግ አተገባበር ስልጠና የሰጠን ሲሆን የምግብ ማበልፀግ ቀደመው የጀመሩ ኢንዱስትሪዎችን ለማበረታታት የገበያ ትስስርና የግንዛቤ ፈጥራ ስራ ተሰርቷል ብለዋል ፡፡

የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር አማረች ባካሎ የነርቭ ዘንግ ክፍተት ችግርን ለመከላከል እና ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎችም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ከተለያዩ ተቋማት የተቋቋመው የቴክኒክ ቡድን አገራዊ ዕቅድ እና የድርጊት መርሃ ግብር አዘጋጅቶ በቅንጅት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።

ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያያት እንደ ሃገር ምርቱ በስፋት ተመርቶ ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆን እስካሁን የነበሩ የቅንጅት ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በውይይቱ የጤና ሚኒስቴር ፣ ባህልና ስፖርት ፣ግብርና ፣ ንግድ፣ ቱሪዝም ፣የህብረተሰብ ጤና ኢኒስትቲውት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

Share this Post