በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ምክንያት አርሶአደሮች ጥቅማቸውን እንዳያጡ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል(አቶ ሀሰን መሃመድ)
የካቲት 12/2018 ዓ.ም (ኢሚ)የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከሞጆ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ፣ ከሎሜ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ እና የዞኑ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት የሞጆ የቆዳ ኢንዱስትሪ ከተማ እና ፓርክ የቅድመ ምስረታ ስራዎችን በተመለከተ የግምገማ መድረክ አካሄደ፡፡
የግምገማ መድረኩን የመሩት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢንዱስትሪ መሰረተ ልማትና ግብዓት ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሀመድ በሞጆ ለሚቋቋሙ የቆዳ ኢንዱስትሪ ከተማ እና ፖርክ ግንባታ መሬታቸው ለልማት የሚውል አርሶ አደሮች ተገቢ የካሳ ክፍያ ከተፈጸመላቸው በኋላ የሚከፈላቸው ገንዘብ ያለአግባብ እንዳይባክንና ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም እንዲያገኙ መንግስት ቅድመ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
የመደመር መንግስት ለዘርፎች እምርታ በሚለው አቅጣጫ መሰረት የኢንዱስትሪያላይዜሽን ስራዎችን በየደረጃው ያሉ የስራ ሀላፊዎች በቅልጥፍና መስራት እንዳለባቸው ያብራሩት አቶ ሀሰን የሞጆ ሌዘር ሲቲ ምስረታ ለአካባቢው ማህበረሰብ መልካም አጋጣሚ እንደመሆኑ መጠን በሚፈጠርላቸው ሰፊ የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን እንደ ማህበረሰብ ሰፊ ጊዜ የመስራት ባህልን ከወዲሁ ማዳበር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የሞጆ ከተማ አስተዳደር አመራሮች በበኩላቸው የሞጆ የቆዳ ኢንዱስትሪ ከተማ እና ፓርክ የቅድመ ምስረታ ተግባራት ወቅት አርሶ አደሮች በቦታው ተገኝተው መሬታቸውን ባለማስለካት ፣ ድንበራቸውን ጠንቅቀው ባለማወቃቸው እና አስፈላጊዉን ሰነድ በወቅቱ አለማቅረብ በስራቸው ላይ ተግዳሮት ፈጥሮባቸው የነበረ ቢሆንም ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ተቀናጅተው በመስራታቸው ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ የሚውሉ መሬቶችን የመለካት ስራ በማከናወን በኩል ውጤታማ ስራ መስራታቸውን ገልጸዋል፡፡
ለቆዳ ኢንዱስትሪ ከተማ እና ፓርክ ግንባታ የተመረጡ ቀበሌዎች ሸራን ዲባንዲባ፣ሞሞ ሾኪ ና ጣፊ አቦ የተባሉ ሶስት ቀበሌዎች ሲሆኑ 178 ሄክታር መሬት ለመለካት ታቅዶ 165 ሄክታር መሬት የመለካት ስራ ተከናውኗል፡፡ይህም አፈፃፀሙን 93% ማሳካት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
በመርሀ ግብሩ በቅድመ ምስረታ ተግባራት
የሞጆ የቆዳ ኢንዱስትሪ ከተማ እና ፓርክ ግንባታ አብዛኛዉ ስራ የተጠናቀቀ በመሆኑ ቀሪ ስራዎች አንዳለቁ የልማት ተነሽዎችን የካሳ ክፍያ እና መልሶ ማቋቋም እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡
ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽንን ለማስፋፋት በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የአካበባቢውን የተፈጥሮ ጸጋ ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ አምራች ኢንዱስትሪ ለማቋቋም በተዋረድ ያሉ የዘርፉ ተቋማት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አቅጣጫ ማስቀመጡ ይታወቃል፡፡