የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች ከጃፓን ኢንዱስትሪዎች ጋራ የሚሰሩበትንና ውጤታማ የሚሆኑበትን መንገድ ከጃይካ ጋር በመተባበር እናመቻቻለን ( አቶ መላኩ አለበል )
የካቲት 26/2018 ዓ.ም (ኢሚ)የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ከጃፓን አለም አቀፍ የልማት ድርጅት ጃይካ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር እስካሁን በተሰሩ ስራዎች እና ወደፊት በሚሰሩ ስራዎች ላይ ተወያዩ።
በውይይቱ ላይ ሚኒስትሩ እንደገለፁት የኢንዱስትሪ ዘርፉ ችግር ፈቺ በጥናት እና ምርምር ላይ የሚያተኩር ቴክኖሎጂን በመጠቀም የግብዓት ብክነትን ፤ ወጪን መቀነስን ፤ በምርት ሰንሰለቱ ላይ ምርታማነትን ከጥራት ጋር በማዋሃድ ተወዳዳሪነትን የሚያጠናክሩ ስራዎች ለማከናወን የሚያስችል የአምራች የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ተሻሸሎ ወደ ስራ ተገብቷል ሲሉ ገልፀዋል ፡፡
አምራች ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ እና የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ለማሳካት ከምንግዜውም በላይ በመንግስት በኩል ትኩረት የተሰጠው እና ዘርፉን የሚከታተል የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስል ተቋቁሞ የመከታተል ፤ የመደገፍ እና የሚስተዋሉ ችግሮችን የመፍታት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ሲሉ ገልፀዋል ፡፡
ከጃፓን አለም አቀፍ የልማት ድርጅት ጃይካ በጋራ የምንሰራቸው ስራዎች በካይዘን የልህቀት ማዕከል ፤ በኢትዮጵያ ታምርት ፤ በጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም አዲስ በሚጀመሩ ፕሮጀክቶች እና የጃፓን የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን የገለፁት አቶ መላኩ ጃይካ በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ችግር ፈቺ ስራዎችን በመስራት በኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ዘላቂ እና የተረጋጋ የኢኮኖሚ እድገት እና ልማት እንዲመጣ እየተሰራ ላለው ስራ እውቅና እንደሚሰጡ ጠቅሰው በቀጣይ በጋራ የምንሰራቸው ስራዎች አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ገልፀዋል ፡፡
በሌላ በኩል የጃፓን አለም አቀፍ የልማት ድርጅት ጃይካ ምክትል ፕሬዝደንት Hara Shohei እንደገለፁት በዋናነት ጃይካ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሚሰራቸውን ፕሮጀክቶች ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀው በካይዘን የሚሰሩ ስራዎችን በማስፋት ከኢትዮጵያ አልፎ ወደ ሌሎች አፍሪካ ሃገር ማስፋት እንፈልጋለን ብለዋል፡፡