የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስል የመስክ ጉብኝት ኢንዱስትሪዎችን ያነቃቃ ነው/አምባሳደር ግርማ ብሩ/
መጋቢት 01/2018 ዓ.ም (ኢሚ)ብሔራዊ የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስል በሸገር ሲቲ፣ ቢሾፍቱ እና አዳማ ዙሪያ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን የጎበኙ ሲሆን በጉብኝቱ የተነሱ ችግሮች እና መፍትሔዎች ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄዷል፡፡
በውይይቱ የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስል እያደረጋቸው ያለው የመስክ ጉብኝት ኢንዱስትሪዎችን ያነቃቃ እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ እና ብሔራዊ የአምራች ኢንዱስትሪው ካውንስል ሰብሳቢ አምባሳደር ግርማ ብሩ ተናግረዋል፡፡
በመስክ ከተጎበኙት ኢንዱስትሪዎች በተለይ የብረት እና የፓኬጂንግ ኢንዱስትሪዎች ተስፋ ሰጪ ስራዎች መታየታቸውን የገለፁት አምባሳደር ግርማ በክልል የሚደረገው ድጋፍ እና ክትትል ስርዓት የሚበረታታ በመሆኑ የድጋፍና ክትትል ስርዓቱ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
አምባሳደር ግርማ እንዳሉት አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍን መደገፍ አስቸጋሪ ቢሆንም በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች መዋቅራዊ በመሆናቸው የሚመለከታቸው ተቋማት በቅንጅት እና በልዩ ትኩረት ምቹ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት አለባቸው ብለዋል፡፡
የኢንዱሰትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በብሔራዊ ካውንስሉ የሚደረገው የመስክ ጉብኝ አምራች ኢንዱስሪዎች በመጠንም ሆነ በአይነት ትልልቅ ኢንዱስሪዎችን እየተፈጠሩ መሆኑን እና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የሚመሯቸው ብሎም ባለቤት የሆኑባቸው ተስፋ ሰጪ ኢንዱስትሪዎችን ማየት ችለናል ብለዋል፡፡
አቶ መላኩ አክለውም ብሔራዊ የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስሉ የሚያደርጋቸው የመስክ ጉብኝቶች ለዘርፉ እድገት እና ተወዳዳሪነት ከፍተኛ ሚና አላቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው የመስክ ጉብኙቱ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በጥልቀት ለማወቅ እድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸው ተቋማቸው ለኢንዱስትሪ በቂ ግብዓት በማቅረብ የምርት ተወዳዳሪነትን በሚያመጣ እና የወደፊት ትስስርን በሚያጠናክር መልኩ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
አቶ አዲሱ አያይዘውም በአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚነሳውን የግብዓት ችግሮችን የግብይት ሂደቱን የአሰራር ችግር በመፍታት የኢንዱስትሪዎቹን ምርታማነት ለማሳደግ በትኩረት እየሰሩ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ በተለይም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና የግብርና ሚኒስቴር ተቀራርቦ በቅንጅት መስራት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገት ብሎም ለሚደረገው መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ወሳኝ በመሆኑ በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡