የአምራች እንዱስትሪ ዘርፉ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው(አቶ መላኩ አለበል)
መጋቢት 9/2018 ዓ.ም (ኢሚ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል የራሽያ ፌዴሬሽን የኢንዱስትሪ እና ንግድ ሚኒስቴር ዴኤታ አሌክስ ግሩዝዴቭ ተቀበለው ስለ ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል ፡፡
ኢትዮጵያ እና የራሽያ ግንኙነት በፖለቲካ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ዘመናት ያስቀጠረ ህዝባዊ መሰረት ያለው በሁኔታዎች የማይለወጥ ስትራቴጂክ ግንኙነት ነው ይህንን ተምሳሌት የሆነ ግንኙነት በንግድ እና በኢኮኖሚ በማስፋት ማሳደግ ከቻልን ሁለቱን አገሮች በጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግ ከዚህም አልፎ በቀጠናው ብሎም በአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ መገባት ይቻላል ሲሉ ገልፀዋል ፡፡
የኢንዱስትሪ ዘርፉ ችግር ፈቺ በጥናት እና ምርምር ላይ የሚያተኩር ቴክኖሎጂን በመጠቀም የግብዓት ብክነትን ፤ ወጪን በመቀነስን ፤ በምርት ሰንሰለቱ ላይ ምርታማነትን ከጥራት ጋር በማዋሃድ ተወዳዳሪነትን የሚያጠናክሩ ስራዎች ለማከናወን የሚያስችል የአምራች የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ተሻሸሎ ወደ ስራ ተገብቷል ሲሉ ገልፀዋል ፡፡
አምራች ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ከምንጊዜውም በላይ በመንግስት በኩል ትኩረት የተሰጠው እና ዘርፉን የሚከታተል የአምራች ንኢዱስትሪ ብሔራዊ ካውንስል ተቋቁሞ የመከታተል ፤ የመደገፍ እና የሚስተዋሉ ችግሮችን የመፍታት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም ማኑፋክቸሪግ ኢንዱስትሪ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ የራሽያ ባለሃብቶች ካላቸው ልምድና እውቀት አንፃር በብረታ ብረት፣ በኬሚካል፣ በፋርማሲና መሰል ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች ላይ ቢሳተፉ በኢትዮጵያ ገበያ ብሎም ሰፊውን የአፍሪካ ገበያ በቀላሉ በመድረስ ውጤታማ መሆን ይቻላል ብለዋል ፡፡
የራሽያ ፌዴሬሽን የኢንዱስትሪ እና ንግድ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አሌክስ ግሩዝዴቭ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ የራሽያ የረዥም ጊዜ ወዳጅ እና አጋር ሀገር መሆኗን ገልፀው ራሽያ ከኢትዮጵያ ጋር ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ያላት ሃገር እንደመሆኗ ሩሲያ ከኢትዮጵያ በግብርና እና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ላይ በግብርና ማሽነሪዎች፣በማዳበሪያ ምርት፣በምግብ ማቀነባበሪያ እና በግንባታ ግብዓቶች ላይ በትብብር እንዲሁም የረጅም ጊዜ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ስራዎችን መስራት እንደሚፈልጉ በመግለፅ የዕውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማስፋት ያለንን ሁለንተናዊ ግንኙነት የበለጠ እናጠናክራለን ሲሉ ገልፀዋል ፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ራሽያ በኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ በመላው አፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖን በማስፋት የአፍሪካ ስትራቴጂ አጋር መሆን ትፈልጋለች ሲሉ ገልፀዋል ፡፡