የግሉ ሴክተር ቴክኖሎጂ ፈጠራ በተላበሰና ዘላቂ እድገትን በሚያመጣ መልኩ የሚመራ መሆን አለበት /አቶ ሀሰን መሀመድ/
መጋቢት 10/2018 ዓ.ም (ኢ.ሚ) በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሰብሳቢነት የሚመራው በኢትዮጵያ በግሉ ዘርፍ ልማት እና ንግድ ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራው የአውሮፓ ህብረት የልማት አጋር ድርጅቶች ቡድን ውይይት አካሄደ ።
የመሰረተ ልማትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ እና የስራ ቡድን አቶ ሀሰን መሀመድ እንደገለጹት የግሉ ሴክተር አለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማጠናከር ቴክኖሎጂንና ፈጠራን በተላበሰ፣ ዘላቂና አካታች በሆነ እድገት መመራት አለበት ብለዋል፡፡
አቶ ሀሰን የስራ ቡድኑ አባላት ለግሉ ሴክተር እድገት የሚያደርጉት ያላሰለሰ ተሳትፎና ቁርጠኝነት ያለው አጋርነት ሀገሪቱ እየተገበረች ላለው ኢኮኖሚያዊ የከፍታ ጉዞ ሚናው ወሳኝ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የውይይት መድረኩ ቅንጅታችን ለማጎልበት እና የሃገራችን የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገት ለማጠናከር እንዲሁም የንግድ ተወዳዳሪነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ የጋራ ቁርጠኝነትን ለማጎልበት እንደሚያግዝም አብራርተዋል፡፡
የሀገሪቱ መንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት የሚገኝውንና የኢኮኖሚ ሽግግር ማዕከል የሆነውን የግሉን ሴክተር ፈጠራን በተላበሰ ዘላቂነት ባለውና በአካታች አድገት የሚመራ መሆን እንዳለበት ጠቅሰው መንግስት ዘርፉን የሚያጋጥሙትን መዋቅራዊ ተግዳሮቶች ለመቅረፍ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸው የገንዘብ አቅርቦትንና ቅልጥፍናን ለማሻሻል በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ስርዓት መዘርጋትን፤ ለኢንቨስተሮች አስተዳደራዊ ሂደቶችን ለማመቻቸትም የተነደፈው የሞሶብ አገልግሎት ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል፡፡
አቶ ሀሰን አክለውም በምርት ተወዳዳሪነት፣ በፋይናንስ አካታችነት እና በአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ድጋፍ በአረንጓዴ ኢንዱስተሪያላይዜሽን፤ ጥራቱን የጠበቀ የመሰረተ ልማት አቅርቦት እና የንግድ ዝግጁነት ላይ የስራ ቡድኑ ቅድሚያ በመስጠት እና በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ገልጸው በውይይቱ የአውሮፓ ህብረት የልማት ምክትል ሃላፊ በሆኑት አና ሊክሲ አማካኝነት ለተሳታፊዎች የስራ ቡድን የማስፈጸሚያ እቅድ እና አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ ቀርቦ ውይይት ተካሄዶበታል፡፡
ውይይቱ ልዩ ልዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ያካተት ሲሆን ከመንግስት ተቋማት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ገቢዎች ሚኒስቴር፣ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና ኢንቨሰትመንት ኮሚሽን የተገኙ ሲሆን ከአውሮፓ ሃገራት የልማት አጋር ድርጅቶች በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር የሆኑትን ማግኑስ ሌናርትሰንን ጨምሮ የጀርመንና የኢንግሊዝ ኢንባሲ ተወካዮች፣ የዩኤን፡ ዩኤንዲፒ፡ ጂአይዜድ፡ ጃይካ ፣ የአለም ባንክ እና የአውሮፓ ህብረት(EU) ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡