የዘርፉ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽንን ማሳደግ ለቆዳ ኢንዱስትሪው ወሳኝ ነው (አቶ መላኩ አለበል)
መጋቢት 24/2018( አ.ሚ) ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ከሁሉም አፍሪካ ቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች ተቋም ተወካዮች ጋር ተቋሙ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር የሚኖረውን ስትራቴጂክ አጋርነት ዙሪያ ውይይት ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት በዘርፉ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽንን ማሳደግ ለቆዳ ኢንዱስትሪው ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
ውይይቱ ሁሉም አፍሪካ ቆዳ እና የቆዳ ዉጤቶች የተሰኘው ተቋም እያከናወናቸው ያሉ እና የታቀዱ ተግባራትን በተለይም የቆዳ እሴት ሰንሰለት ልማትን በመደገፍ እና በአፍሪካ ከአፍሪካ አህጉር ጋር የተገናኙ ውጥኖችን ወደ ኢትዮጵያ እና ወደ ፊት ወደ ሌሎችም ሀገራት ለማሳደግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስለ የሁሉም አፍሪካ ቆዳና የቆዳ ዉጤቶች ተቋም ፕሮግራሞች እና ስትራቴጂካዊ አስተዋፅኦዎች ጠለቅ ያለ ግንዛቤ በማግኘት ትብብርን ለማጠናከር እና ኢትዮጵያ ከኢንስቲትዩቱ ጋር ያላትን ተሳትፎና ድጋፍ ለማሳለጥ ያለመ ነው።
የኢንዱሰትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በዘርፉ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን አቅማችን የአለም የቆዳ እና ቆዳ ዉጤቶች ከደረሰበት ደረጃ አለመድረሱ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሆነ እና በፍጥነት ዓለም ከደረሰበት ደረጃ መድረስ ካልተቻለ በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳደሪነታችን ስለሚያሳጣን የተለያዩ እና ቀጣይነት ያላቸው ውይይቶችን በማዘጋጀት በዘርፉ ያሉብንን ተግዳሮቶች ለይተን ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሽግግር ላይ መስራት አለብን ብለዋል፡፡
በውይይቱ የቆዳ ኤክስፖርት ስትራቴጅን ለማጠናከር፤ዘርፉን ዉጤታማ ለማድረግ፤ የክላሰተር ልማትን፤ የቆዳ ፋብሪካዎችንና ሸቀጦችን፤ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተረፕራይችን በማዋሃድ ዘላቂ ኢንቨሰተመንትን ለማበረታታት፤ የዉጭ ቀጥታ ኢንቨሰትመንትንና የሀገር ዉስጥ ኢንቨስትመንትን ለማጠናከር፣ ዘላቂ የግብዓት አቅርቦትን ለማሻሻልና የቴክኖሎጂ አቅምን ለማሳደግ የገበያ ተወዳዳሪነት ላይ ሊሰራ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
የሁሉም አፍሪካ ቆዳ እና የቆዳ ዉጤቶች ተቋምና ሚኒሰቴር መስሪያ ቤቱ በማኔጅመንት ግንባታ ፕሮግራም ፤ በቆዳ አና የቆዳ ዉጤቶችን በማደስ፤ የምርምርና ልማት ማዕከልን በማጠናከር እና በስልጠና በትብበር ሊሰሩባቸው የሚገቡ መስኮች አንደሆኑ በውይይቱ ተነስቷል፡
የሁሉም አፍሪካ ቆዳ እና የቆዳ ዉጤቶች ኤክስኩቲቭ ዳይሬክተር ኒኮላስ ሙዱንዌ የአለም አቀፍ ሌዘር አሴት ሰንሰለት እና የአፍሪካ አስተዋጽኦ አለም አቀፋዊ ተለዋዋጭ ሁኔታ እና በዘርፉ የሚያሰከትላቸው ዋና ዋና የሆኑ ስጋቶች እና በዘርፉ በ2026 በኢትዮጵያ ሰለሚተገበሩ ዝርዝር ተግባራትን የሚመለከቱ ዶክመንት አቅርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒሰቴር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፡ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት እና የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ የምርምርና ልማት ማዕከል ኃላፊዎች እና የሁሉም አፍሪካ ቆዳ እና የቆዳ ዉጤቶች ተቋም ተወካዮች በምክክሩ ተሳትፈዋል፡፡