አረንጓዴ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ምኞት ሳይሆን ለሁኔታዎች የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ስልታዊ መንገድ ነው (አቶ ሀሰን መሐመድ )
መጋቢት 26/2018 ዓ.ም (ኢሚ) የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሐመድ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን አስመልክቶ የኢንዱስትሪ ሽግግር መሪዎች ቡድን የስትኮልም የአካባቢ ጥበቃ ኢንስቲትዩት (Stockholm environment institute and leadership Group for industry transition ባዘጋጀው ውይይት ላይ ተሳትፈዋል፡፡
በውይይታቸው የሚወሰኑ ውሳኔዎች ለቀጣይ ትውልድ ተሻጋሪ ናቸው ያሉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን የኢንዱስትሪያላዜሽን ጉዞዋችን ያለፈውን አይነት አካሄድ የማይከተል ይልቁንም በአዲስ መልክ ኢኮኖሚያዊ ፍላጎትን ከአካባቢያዊ ኃላፊነት ጋር ያጣመረ መሆን አለበት ሲሉ ገልጸዋል፡፡
እንደ ሀገር ወደ ኢንዱስትሪያላዜሽን የምናደርገው ጉዞ ወሳኝ ወቅት ላይ እንገኛለን ያሉት አቶ ሀሰን ተግባራዊ ያደረግነው መዋቅራዊ ሽግግር እና የኢኮኖሚ ዕድገት በአለም አቀፍ ደረጃ የካርበን ልህቀት መጠንን ለመቀነስ የሚደረገውን ጉዞ ፈታኝ ብቻ ሳይሆን ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግም በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ፣ምርታማ ብቻ ሳይሆን ጠንካራ፣ አካታች እና ለሁኔታዎች የማይበገር ኢኮኖሚ የመገንባት ዕድልን ያገናዘበ በመሆኑ ታሪካዊ አጋጣሚም ጭምር ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ለኢትዮጵያውያን የአረንጓዴ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ረቂቅ ምኞት ሳይሆን ለሁኔታዎች የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ስልታዊ መንገድም ነው ያሉት አቶ ሀሰን ለዜጎች የስራ እድልን ለመፍጠር፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ፣ ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት እና የዛሬው ልማት የነገውን ብልጽግና እንዳይጎዳ ማድረግ መሆኑንና ለዚህም ኢትዮጵያ በሴፕቴምበር 2025 ላይ የኢንዱስትሪ ልማትን ከአየር ንብረት ተቋቋሚነት እና ከማህበራዊ ፍትሃዊነት ጋር ለማጣጣም ያላትን ቁርጥ አቋም ያንጸባረቀ ነው ሲሉ አቶ ሀሰን መሀመድ አክለዋል፡፡
ይህን ራዕይ ወደ ተግባር ለመተርጎም የተወሰዱ እርምጃዎችን በተመለከተም የለውጥ እቅድ ተዘጋጅቶ በከፍተኛ አመራሩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተመራ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው የኢንዱስትሪዎችን የኃይል መሰረት መለወጥ ፣ ብቁና ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን ለካርቦናይዜሽን በመሰረትነት መጠቀም እና በሰው አቅም እና ተቋማዊ ጥንካሬ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ሀገር በካርበን ልቀት ሂሳብ አያያዝ፣ የግሪን ሃውስ ጋዝ ግኝቶች እና የሰርኩራል ኢኮኖሚ ልምምዶች ላይ ያለንን አቅም እያጠናከርን ነው ያሉት አቶ ሀሰን እነዚህ ጥረቶች እድገታችንን ሊለካ የሚችል ግልጽና ከአለም አቀፍ ደረጃዎች ጋር የተጣጣመ መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የዝቅተኛ የካርቦን ልቀት የኢንዱስትሪ ስርዓት ሽግግርን በማድረግ ላይ ባሉ ሀገራት ለማምጣት የአጋር አካላትን ድጋፍ ይጠይቃል ያሉት አቶ ሃሰን በዚህም መሰረት የስዊድን መንግስት፣ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ፣የስዊድን ስቶኮልም የአካባቢ ኢንስቲትዩት እና ለኢንዱስትሪ ሽግግር አመራር ቡድን (LeadIT) እና ሰፊው አለም አቀፍ ማህበረሰብ የፖሊሲና ኢንቨስትመንት በማጠናከር፣ የቴክኒክ ድጋፍን በማጠናከር እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማመቻቻት ረገድ ያላቸውን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡