አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጅ የጀርባ አጥንት ናቸው

መጋቢት 30/2018 ዓም(ኢ.ሚ) የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ፕሮጀክት ኢፒሳ ኢንጅነሪንግ ካምፓኒ (IPISA) ከተባለ የስፔን አማካሪ ድርጅት ጋር አብሮ መስራት የሚያስችል የመግባቢያ የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ፡፡

በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መሰረተ ልማትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሃመድ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ የጀርባ አጥንት ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡  አቶ ሀሰን ከኢፒሳ ጋር በትብብር መስራት በሁሉም ክልሎች የአግሮ ኢንዱስትሪውን ስነ ምህዳር በማጠናከር ኢትዮጵያ እያደረገች ላለችው ሁሉን አቀፍ አካታች የኢኮኖሚ ዕድገትና የኢንዱስትሪያላይዜሽን ጉዞ የጎላ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አርሶ አደሩን፣ የፋብሪካ ባለሀብቶችን፣ የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢ አምራቾችንና ኤክስፖርተሮችን በአንድ ስነ ምህዳር ያገናኛል ያሉት ሚንስትር ዴኤታው ፓርኮቹ ግብርናን በቀጥታ ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር ስለሚያገናኙ ከምርት በኋላ የሚከሰት የምርት ብክነትን ከማስቀረት ባሻገር የዕሴት ጭማሪ ስራዎችንና ሀገር በቀል የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን የመጠቀም ልምድን በማዳበር ረገድ ክፍተኛ ጥቅም እንደሚኖራቸው ተናግረዋል፡፡  የኢፕሳ ምስራቅና መካከለኛ አፍሪካ ስራ አስኪያጅ ሚስተር ፔትሮ ፍራንሲስኮ በበኩላቸው ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በሚኖራቸው የስራ አጋርነት ቆይታ ካምፓኒያቸው ያካበተውን ልምድና ዕውቀት በማሸጋገር ለኢትዮጵያ አግሮ ኢንዱስትሪ እድገት የራሱን አሻራ ለማስቀመጥ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ፕሮጀክት ጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ አያልነህ አባዋም ፕሮጀክቱ ላለፉት ሁለት ዓመታት ዓለም አቀፍ ጨረታ በማውጣት የተለያዩ ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅቶችን ሲያወዳድር መቆየቱን ገልጸው የአፍሪካ ልማት ባንክን መስፈርት ስላሟላ ኢፒሳን ማሳለፋቸውን አብራርተዋል፡፡

የስምምነቱ ዋና ዓላማ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለሚያስገነባቸው አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ዝርዝር ዲዛይን እና የአዋጭነት ጥናት ማሰራት ሲሆን ኢፒሳም በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስራውን አጠናቆ እንደሚያስረክብ ይጠበቃል፡፡

Share this Post