የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ሚና እያበረከተ ይገኛል
የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ሚና እያበረከተ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 25/2018 (ኢዜአ)፦የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ረገድ ትልቅ ሚና እያበረከተ ይገኛል ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሀሳብ አራተኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ዓለም አቀፍ ኤክስፖ አስጀምረዋል።
በኤክስፖ መክፈቻ ሥነ ስነ ሥርዓት ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምኅረት፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በወቅቱ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ በመደመር መንግሥት ኢትዮጵያ ያላትን አምራች የሰው ኃይል ተጠቅማ የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ረገድ እየታዩ ያሉ ተጨባጭ ውጤቶች፣ ሀገሪቷ ከጀመረችው የብልጽግና ጉዞ ምንም የሚያስቆማት ነገር እንደሌለ ማሳያ ነው።
በመደመር እሳቤ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የኢንዱስትሪው ዘርፍ ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመዋል።
የመደመር መንግሥት ኢንዱስትሪን የሚመለከተው ለሀገር ከሚኖረው ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ባሻገር የሀገር ሉዓላዊነትን ከማስጠበቅ፣ ከጥገኝነት ተላቆ ራስን ከመቻል እና ከሀገራዊ ክብር ጋር መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ነው የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ያረጋገጡት።