የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ከዱባይ ቻምበርስ ፕሬዘዳንት ሙሃመድ ሎታህ ጋር ተወያዩ
ግንቦት 13/2018 ( ኢ.ሚ) የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል የዱባይ ቻምበርስ ፕሬዘዳንት ሙሃመድ ሎታህን ጨምሮ ከዱባይ ቻምበርስ የመጡ ልኡካን ቡድን አባላትን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው በሁለቱ ሃገራት መካከል እያደገ የመጣውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት በሚመለከት ውይይት አካሂደዋል፡፡
በውይይታቸውም ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ኢትዮጵያ ያላት የሰው ሃይል፣ የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ፣ ሁሉንም አይነት የግብርና ምርቶች ማምረት መቻሏ፣ በጠንካራ የንግድ ነፃነት የሚመራው በአፍሪካ ትልቁ እና ትርፋማ የሆነው ከ150 በላይ አውሮፕላኖች ያሉትና ከ180 በላይ አለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ መዳረሻዎች ያለው አየር መንገድ ባለቤት መሆኗ፣ ከሌሎች ሃገራት ጋር ሲነጻጸር የሃይል ዋጋ ርካሽነት እና ከሁሉም በላይ መንግስት ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የሰጠው ልዩ ትኩረት ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ ምን ያህል ምቹ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
የዱባይ ቻምበርስ ፕሬዘዳንት ሙሃመድ ሎታህ በበኩላቸው በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እያደገ የመጣውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት አድንቀው ውደፊትም በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ የቻምበርሱን ፕሬዘዳንት መሃመድ ሉታህን ጨምሮ ምክትል ፕሬዘዳንቱ ሳሌም አል ሻምሲ፡የአፍሪካ ዳይሬክተር መሃመድ አል አታታር ፣ በዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር ጀማል በክሪ፣ የቻምበርሱ የኢትዮጵያ ተወካይ መላኩ ጁሃር እና ሌሎችም አባላት ተገኝተዋል፡፡