የሞጆ ሌዘር ሲቲ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ከጥሬ ቆዳ ኤክስፖርት ወደ ላቀ እሴት የተጨመረባቸው የተጠናቀቁ ምርቶች ማምረቻነት በመቀየር የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ያሳድጋል (አቶ ሀሰን መሀመድ)

ሰኔ 12/2018 (ኢ.ሚ)ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች በሞጆ ሌዘር ሲቲ ፕሮጀክት እና የኢንዱስትሪዎችን የስራ እንቅስቃሴ የመስክ ምልከታ አደረጉ፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሃመድ የሞጆ ሌዘር ሲቲ በ13.5 ቢሊየን ብር በፌደራል መንግስት የሚገነባ ሀገራዊ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸው ይህ በአይነቱ ልዩና ግዙፍ የሆነ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የአካባቢውን ኢኮኖሚ እንደሚያነቃቃና ለአካባቢው ማህበረሰብ ትልቅ ጥቅም እንደሚሰጥም አብራርተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የአካባቢውን ማህበረሰብና በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሀብቶችን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ረጅም ታሪክ ያለውን እና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ እምቅ አቅም የያዘውን የኢትዮጵያን የቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች የምርት ዘርፉን ከጥሬ ቆዳ ኤክስፖርት ወደ ላቀ እሴት የተጨመረባቸው የተጠናቀቁ ምርቶች ማምረቻነት በመቀየር የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከማሳደጉም በላይ ለሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር እና ዓለም አቀፍ ባለሀብቶችን በመሳብ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ፋይዳው የጎላ ሜጋ ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡

ሚኒስትር ድኤታው አክለውም በአጭር ጊዜ ውስጥ የካሳ ክፍያው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ዲዛይንና ግንባታ ስራ እንደሚገባ እና በተዘጋጀው የመልሶ መቋቋም መመሪያ መሰረት ከቦታው ለተነሱ አርሶ አደሮች የህይወት ማሻሻያ ስራዎች የማከናወን ስራው በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተው ለዚህ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክት ስኬት የወረዳው አመራሮችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በመስክ ምልከታው የሞጆ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ የወረዳው ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

Share this Post