የኢትዮጵያ መንግስት ቴክኖሎጅን በማላመድና ምርትን በማሻሻል የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማዘመን ቁርጠኛ ነው( አቶ ታረቀኝ ቡልልታ)
ሰኔ19/2018 ዓ.ም (ኢሚ) የኢፌድሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት በአፍሪካ ቀጣይነት ያለው የቆዳ ኢንዱስትሪ ዕድገት ለማምጣት ያለመ ወርክ ሾፕ አካሄደ፡፡ በመርሀ ግብሩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢንዱስትሪ ዕድገትና ተወዳዳሪነት ዘርፍ ሚንስትር ደኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ የኢትዮጵያ መንግስት አዳዲስ ቴክኖሎጅዎችን በማላመድና ምርትን በማሻሻል የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማዘመን በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ ታረቀኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ከቆዳ ኢንዱስትሪ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የአካባቢ ብክለት ችግሮችን ለመፍታት ቀጣይነት ያለው የአመራረትና ፀረ ብክለት ፕሮጀክት( sustainable manufacturing& environmental pollution project) እየሰራ ያለው ስራ ለዘርፉ መዘመን ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የቆዳ ዘርፍ በኢትዮጵያ እንደ ዋነኛ ስትራቴጅክ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ መለየቱን የጠቀሱት ሚንስትር ዴኤታው አፍሪካ ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ያላት አህጉር እንደ መሆኗ መጠን የዘርፉ መዘመን ለስራ ዕድል ፈጠራ፣ ከወጭ ንግድ ና ከኢንዱስትሪ ሽግግር አኳያ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም ፕሮጀክቱ የቆዳ ተረፈ ምርቶችን ወደ ጠቃሚ የግብርና ግብዓቶች ለመቀየር ያካሄደው ምርምርና በቆዳ ፋብሪካዎች የቆዳን ፀጉር የአካባቢ ብክለትን በማያመጣ ኢንዛይም ከማስወገድ አንጻር እየሰራ ያለው ስራ ቀደም ሲል ከአካባቢ ብክለት ጋር ተያይዞ በማህበረሰቡ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን በመፍታት አረንጓዴ ኢንዱስሪያላይዜሽንን ዕውን በማድረግ ረገድ የሚያበረታታ ውጤት እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህም ኢትዮጵያ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የኡደታዊ ኢኮኖሚን ጽንሰ ሀሳብ ለማስፋፋት ያላትን ርዕይ እያሳካ ነው ብለዋል፡፡
በመርሀ ግብሩ ያለ በካይ ኬሚካሎች የቆዳ ኢንዱስትሪ አሰራርና የአረንጓዴ የቆዳ ኢንዱስትሪያላይዜሽንን በተመለከተ ያሉ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች በከፍተኛ ባለሙያዎች ገለጻ ተደርጎባቸው ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን በመርሃ ግብሩ ከፍተኛ የዘርፍ ባለሙያዎች ፣የሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ የልማት አጋር ድርጅቶችና የቆዳ ዘርፍ ማህበራት ተወካዮች ተሳትፈውበታል፡፡