ኢትዮጵያ በአረንጓዴ የኢንዱስትሪ ልማት ዓለም አቀፍ ተምሳሌት ለመሆን እየሰራች ነው

ሰኔ 19/2018 ዓ.ም (ኢሚ) የአየር ንብረት ለውጥ ሳምንት (London Climate Action Week) አካል ሆኖ በተካሄደው "የአለም አቀፍ አረንጓዴ ኢንዱስትሪ ኮንፈረንስ" ላይ ኢትዮጵያ ያላትን የላቀ የኢንዱስትሪ የአየር ንብረት ጥበቃ ቁርጠኝነት ይፋ አደረገች።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የመሰረት ልማትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪ ልማት የምትጠቀመው የኤሌክትሪክ ኃይል ከዓለማችን ንጹህ ከሚባሉ የኃይል ምንጮች መካከል እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

አገሪቱ በውኃ፣ በንፋስ፣ በፀሐይ እና በጂኦተርማል ኃይል ላይ የተመሰረተ ኢንዱስትሪያዊ ዕድገት እያስመዘገበች መሆኗን ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው በንግግራቸው ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢንዱስትሪ አብዮት ያላትን እቅድ አስመልክተው የአየር ንብረት ተቋቋሚ አረንጓዴ ኢኮኖሚ፡ ኢትዮጵያ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ራዕይ በመከተል፤ እንደ "አረንጓዴ አሻራ"፣ "በኢትዮጵያ የተሰራ" ኢትዮጵያ ታምርት(Made in Ethiopia) ንቅናቄ እና የኢ-ሞቢሊቲ ፕሮግራሞችን በማቀናጀት ዘላቂ ኢንዱስትሪያዊ ዕድገትን እያረጋገጠች ትገኛለለች ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ቀስ በቀስ በአረንጓዴ ኃይል የሚንቀሳቀሱ፣ ሀብትን በአግባቡ የሚጠቀሙ እና የፈጠራ ስራዎችን የሚያበረታቱ የልማት ማዕከላት እየሆኑ መምጣታቸውን የጠቀሱት ሚስትር ዴኤታው ዘላቂ የሆነ የኢንዱስትሪ ሽግግር በአንድ አገር ብቻ የሚሳካ አለመሆኑን፤ የተሻለ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የፋይናንስ ድጋፍ እና አገር በቀል አመራር የተላበሱ ዓለም አቀፍ አጋርነቶች ወሳኝ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል።

Share this Post