በአምራች ዘርፍ ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ዕድገት ዘለቂ መፍትሔ ያመጣል (አቶ መላኩ አለበል)

ሰኔ 29/2018 ዓ.ም (ኢሚ) የአምራች ኢንዱስትሪ ብሔራዊ የሀብት ልየታ ጥናት የትግበራ ይፋዊ ማስጀመሪያ መድረክ የክልል ፕሬዝዳንቶች በተገኙበት ተካሄዷል።

በመድረኩ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል እንደገለፁት የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ዕድገትና ልማት ቀጣይነት ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው።

በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ያሉ እምቅ ሃብቶችን በመለየት ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል የብሔራዊ አምራች ኢንዱስትሪ የሃብት ልየታ ጥናት መሆኑን ተናግረዋል ።

ጥናቱ ከሌሎች የኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች ጋር በግብዓትና በምርት አቅርቦት ሊደርግ የሚችለውን ትስስር በመደጋገፍ ውጤታማ የኢንቨስትመንት በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ማሳካት እንደሚቻል ጠቁመዋል።

ጥናቱ በአምራች ዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ አካላት በምን ዘርፍ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ምክረ ሃሳብ ለመስጠት ያግዛል ያሉት ሚኒስትሩ በተለይም ደግሞ ለኢንዱስትሪ ማደግና መልማት በአገራችን በሁሉም የክልል እና ከተማ አስተዳደሮች ያሉ እምቅ ሀብቶችን በውል አውቆና ለይቶ ጥቅም ላይ ለማዋል ጥናቱ መልስ አንደሚሰጥ አስረድተዋል።

በጥናቱ እንደ አካባቢዎቹ አቅም የኢኮኖሚ ኮሪደሮች የተለዩ መሆናቸውን ያነሱት አቶ መላኩ አለበል በአምራች ዘርፍ ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ዕድገት ዘለቂ መፍትሔ አንደሚመጣ ገልፀዋል።

የክልል ፕሬዝዳንቶች፣ የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ ሚኒስትሮች፣ሚኒስትር ዴኤታዎች እና የዘርፋ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት አመራሮች የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተዋል።

Share this Post