የኢትዮጵያ መንግስት ለውጭ ኢንቨስተሮች ምቹና ሳቢ የሆነ የስራ አካባቢ ለመፍጠር ቁርጠኛ ነው
የኢፌድሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በጨርቃጨርቅ ዘርፍ አምራች ኢንዱስትሪዎችን የምርት ጥራት የሚጠበቅበትን ሁኔታ አስመልክቶ አሬና(ARENA) ከተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር ተወያየ፡፡
ውይይቱን የመሩት የኢንዱስትሪ መሰረተ ልማትና ግብአት ዘርፍ ሚንስትረ ደኤታ አቶ ሀሰን መሐመድ መንግስት ለውጭ ኢንቨስተሮች ምቹና ሳቢ የስራ አካባቢ ለመፍጠር ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መንግስት ኢትዮጵያን የአፍሪካ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ መዳረሻ ለማድረግ አልሞ እየሰራ መሆኑን ያብራሩት አቶ ሀሰን ሀገሪቱ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን ያሟሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮችንና ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ከሟሟላት በተጨማሪ በርካታ አምራች ወጣት የሰው ሀይልና የታዳሽ ኢነርጅ ባለቤት መሆኗን አስረድተዋል፡፡
በመርሀ ግብሩ ሀገሪቱ ያሏት የኢንቨስትመንት አማራጮች የተገለጹ ሲሆን አሁን ላይ የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ስላለበት ሁኔታ፣ ከጉምሩክ ጋርና ከታክስ ጋር ተያይዞ መንግስት ስላደረገው ማሻሻያ፣ የባቡር ካርጎ ፣የኤሌክትሪክ ሀይል፣ ዓለም አቀፍ የንግድ ስምምነቶችና ና አጠቃላይ መንግስት የሰራቸውን የሪፎርም ስራዎች አስመልክቶ ሰፊ ውይይት ተካሄዷል፡፡
በውይይቱ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ፣ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ፣ከጅ አይ ዜድ እና ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት ተሳትፈዋል፡፡