ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት የግሉ ዘርፍ መልማት ፋይዳው ከፍተኛ ነው

ሀምሌ 2/2018 ዓ.ም (ኢሚ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የግብዓትና መሰረተ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሃሰን መሃመድ፤ ከስዊድን ኤምባሲ ከፍተኛ የፕሮግራም ማናጀር ሚስዝ ኒኮላ) እና ከኢኮኖሚ፣ ንግድና የግል ዘርፍ ልማት ፕሮግራም ኦፊሰር አቶ አድሪያን ካኖ የስራ ቡድኑ ጋር በጋራ የሚሰሩ ስራዎች ላይ እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል ።

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሃሰን በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት የግል ዘርፍ ልማት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት ያለውን ከፍተኛ ፋይዳ ገልጸው፤ የተመሰረተው የጋራ የስራ ቡድን የሀገሪቱን የ10 ዓመት የልማት እቅድ እና የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳን ለመደገፍ ትልቅ አቅም መሆኑን ጠቁመዋል ።

መንግስት ለግል ዘርፉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝና ከልማት አጋሮች የሚጠበቀው ድጋፍም ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የስዊድን ኤምባሲ ከፍተኛ የፕሮግራም ማናጀርሚስዝ ኒኮላ ፋኬል (Mrs. Nicola Fackel) በበኩላቸው በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋና አቀርበው በተቋሙ እየታየ ያለውን ለውጥ አድንቀዋል ።

ከዚህ በፊት የተደረጉ ውይይቶችን መለስ ብሎ መገምገምና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በግልጽ ማስቀመጥ ለጋራ የስራ ቡድኑ ስኬት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው በቅርቡ የስራ ኃላፊነታቸውን ለምተካው አዲስ ባልደረባቸው አኒካ ጉስታፍሰን ስራዎችን በተሳለጠ ሁኔታ ለማስረከብ እንዲቻል፣ የጋራ የስራ ቡድኑን የቀጣይ ጊዜያት የተግባር መርሃ-ግብር እና የማጣቀሻ ውሎችን (Terms of Reference) በግልጽ መለየት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

አያይዘውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና በልማት አጋሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ፣ መረጃ ከመለዋወጥ ባለፈ ወደ ተግባራዊ የጋራ ፈጠራ ሂደት (Co-creation process) ሊሸጋገር እንደሚገባና የሚጠበቁ ውጤቶችንም በቅንነትና በግልጽነት ማስተናገድ እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተው ገልፀዋል ።

Share this Post