የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ከኢንዱስትሪ ዘርፍ ጋር ያላቸውን ጥምረት ሊጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ 10/10/2014 ዓ.ም (ኢሚ) የማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል በተመረጡ ኢንዱስትሪዎች ከአንድ አመት በላይ ላሰለጠናቸው የኮሌጅ አሰልጣኝ መምህራን እውቅና ሰጥቷል፡፡

በኢንዱስትሪው ዘርፍ በዕውቀትና ክዕሎት የዳበረ አምራች ኃይል በማፍራት ረገድ እንደ ሀገር ክፍተት መኖሩ የገለጹት የማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂውና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው ረጋሳ ይህ አይነቱን ችግር ለመቅረፍ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ከኢንዱስትሪው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በሥራ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍና በዘርፉ በዕቅቀትና ክህሎት የዳበረ አምራች ኃይል ለመፍጠር የትምህርት ተቋማትንና አምራች ኢንዱስትሪን የሚያስተሳስር ፕሮግራም ተቀርጾ ወደ ስራ መገባቱን ያስረዱት ዋና ዳይሬክተሩ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት መምህራን /አሰልጣኞች የዘርፉን ነባራዊ ሁኔታ እንዲገነዘቡና ያለባቸውን የዕውቅት ክህሎት ክፍተት በመሙላት ኢንዱስትሪው በሚፈለገው ልክ ለማብቃት ወደ ስራ መገባቱን ገልፀዋል ።

የምርምር ማዕከሉ ከህፃናት አድን ድርጅት ባገኘው የፋይናስ ድጋፍ ከአራዳ ማኑፋክቸሪንግ፣ የካ ኢንዱስሪያል እና ተግባረ ዕድ እንዲሁም ከጄነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ለተውጣጡ 120 የኮሌጅ መምህራን/ አሰልጣኞች በአራት ዙር ለአስራ አምስት ወራት በተግባር የተደገፈ ስልጠና መሰጠቱን አቶ አስፋው ጠቁመዋል ።

ይህ አይነቱ ስልጠና የኢንዱስትሪ ዘርፉን አቅም በማጎልበት ረገድ አዎንታዊ ሚና የሚጫወት በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ቀጣይነት ባለው መልኩ ትኩረት ሰጥው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ተግባር ተኮር ስልጠናው በማኑፋክቸሪንግ፣ ኤሌክትሪክ፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ በአውቶሞቲቭ እና አሉሚኒየም የስራ ዘርፎች ላይ ማተኮሩም ተገልጿል፡፡

Share this Post