ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የምርት ውጤታማነት የማምረት አቅም አጠቃቀም ልኬት ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ 13/01/2015 ዓ.ም (ኢሚ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተኪ ምርቶች ተወዳዳሪነት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ሺበሺ ስዩም እንደገለፁት የማምረት አቅም አጠቃቀም ልኬት የአምራች ኢንዱስትሪዎችን በምን ያህል ደረጃ ተጠቅሞ ምርት አምርቷል የሚለውን በመቶኛ የሚገልጽ ሲሆን ቁልፍ የአፈጻጸም አመላካች ከሚባሉ መለኪያዎች ውስጥ አንዱና ዋንኛው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የማምረት አቅም አጠቃቀም በብዛት ማምረትን ብቻ ሳይሆን የሚፈለገውን ያህል ለማምረት አምራች ኢንዱስትሪው ምን መስራት እንዳለበትም የሚያግዝ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በተመረተ ምርትና ሊመረት የሚችል ምርት አቅም ጋር ያለውን ግንኙነት ባለፈ የምርቱ ፍላጎት በገበያ ምን እንደሚመስል ደረጃውን ለማወቅም የሚረዳ ሲሆን አነስተኛ ካፒታል እና በጣም ዝቅተኛ አቅም አጠቃቀም ያላቸው እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በዓለም ገበያ ተፈላጊ ምርቶችን በማምረት ተወዳዳሪ ለመሆን እንዲችሉ የማምረት አቅም አጠቃቀም ልኬት ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አምራች ኢንዱስትሪው በምርት ማምረት ሂደት ውስጥ የግብአት አጠቃቀም ውጤታማነት እንዲሁም በግብአትና ምርት መካከል ያለውን ተዛማጅነት እና የፍጆታ ምጣኔ የሚለካበት ዘዴ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የአቅም አጠቃቀም ልኬት አምራች ኢንዱስትሪውን ወደ ትክክለኛ ውጤት እንዲደርስ ሁሉም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ አቶ ሺበሺ ስዩም አሳስበዋል፡፡

Share this Post