አዲሱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ለአገር ውስጥ አምራቾች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል( ክቡር አቶ መላኩ አለበል)
ታህሳስ 18/2016 ዓ.ም (ኢሚ) ከ20 ዓመታት በላይ ሲያገለግል የቆየውን የኢንዱስትሪ ስትራቴጅ ክፍተቶች በማሻሻል፣ በዘርፉ ውጤታማ የሆኑ በርካታ ሀገራትን ተሞክሮ በማካተትና ዘመኑ የሚጠይቀውን የአምራች ኢንዱስትሪ ጥያቄ ሊመልስ በሚችል መልኩ ተዘጋጅቶ ፀድቆ ወደ ስራ የገባው አዲሱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ለአገር ውስጥ አምራቾች ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ክቡር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።
ሚኒስትሩ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውና የ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ለአምራች ኢንዱስትሪው ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው 5 ዘርፎች አንዱ መሆኑ ለዘርፉ መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።
መንግስት ለዘርፉ መጠናከር የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው ያሉት አቶ መላኩ፤ ከዓለም አቀፋዊና አገራዊ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ አዲስ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ወደ ስራ ማስገባቱን ገልጸዋል።
አዲሱ የኣንዱስትሪ ፖሊሲ ላለፉት 20 ዓመታት ሲተገበር የቆየው የዘርፉ ስትራቴጅ ላይ የነበሩ ክፍተቶችን በሚደፍን መልኩ መዘጋጀቱን የጠቆሙት ሚኒስትሩ የቴክኖሎጂ እድገትን፣ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑይም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት የተፈጠሩ መልካም የቅንጅትና የጋራ ስራዎችን በማጠናከር ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥማቸውን የግብዓት፣ የኃይልና የፋይናንስ ችግሮች ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
በፋይናስ አቅርቦት ላይ የነበረውን ችግር ለመፍታት ባንኮች ከፍተኛውን የብድር መጠን ለግል ዘርፉ እንዲሰጡ መደረጉ ችግሩን እያቃለለ መሆኑን የጠቀሱት አቶ መላኩ ለአብነትም ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ለኢንዱስትሪዎች 266 ሚሊዮን ዶላር ብድር መቅረቡን ገልፀዋል።
የኢንዱስትሪዎቹ የማምረት አቅም በ2013 ዓ.ም ከነበረበት 46 በመቶ አሁን ላይ ወደ 56 በመቶ ከፍ ማለቱን ጠቅሰዋል።
በአምራች ኢንዱስትሪ ፓርኮች የመስሪያ ቦታ ከወሰዱ 127 አምራቾች ግማሹ የአገር ውስጥ መሆናቸውን የገለፁት ሚኒስትሩ ገቢ ምርቶችን ለመተካት ሰፊ ስራ እየተሠራ በሆኑና ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ በመሆኑ የመንግስት ተቋማት የአገር ውስጥ ምርቶችን እንዲገዙ ከማድረግ ጀምሮ በርካታ ማበረታቻዎች እየተደረጉ ነው ብለዋል።
#ኢትዮጵያ_ታምርት
#እኛም_እንሸምት