በደብረ ብርሃን ከተማ አራት የተለያዩ ፋብሪካዎች ተመረቁ

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን፥ "አባቶቻችን በደማቸው የዓድዋ ድልን አምጥተዋል፤ እኛ ደግሞ ልማትን በላባችን ማስመዝገብ አለብን" ብለዋል።

ፋብሪካዎች መሠረታቸው መሬት ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳደድሩ፤ "ዛሬ የመረቅናቸው አምራች ኢንዱስትሪዎች የአካባቢውን ምርት በግብዓትነት መጠቀማቸው ጠንካራ የገበያ ትስስር እንዲኖር ያደርጋል" ብለዋል።

በዛሬው ዕለት የተመረቁት ዛሙ ኤምዲኤፍ ማምረቻ፣ ጅንሹ ኢትዮጵያ ቴክስታይል ቴክኖሎጂ ክር ማምረቻ፣ ሂንድ ፕላስቲክ ማኑፍክቸሪንግ እና ሊሃም ትሬዲንግ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የሀገር ውስጥ ጥሬ ዕቃ ተጠቅመው የውጭ ምንዛሬ በማዳን በኩልም ሚናቸው የጎላ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከተማዋ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ያላት ምቹነት እና ተመራጭነት በሰላም እና ደኅንነትም ሊረጋገጥ እንደሚገባ የገለጹት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ፤ ለዚህም ማኅበረሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

እንደ አሚኮ ዘገባ፥ በደብረ ብርሃን ከተማ በተያዘው በጀት ዓመት 17 አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንደሚገቡ ይጠበቃል።

10 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያላቸው እነዚህ ኢንዱስትሪዎች፥ ለ3 ሺህ 100 ነዋሪዎች የሥራ እድል ይፈጥራሉ።

መረጃው፦ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ነው።

ይከታተሉን

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post