በቆዳው ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የውይይት መድረክ ተካሄደ

ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የካቲት 27/2016 ዓ.ም በቆዳ ኢንዱስትሪው ዘርፍ በሚታዩ ወቅታዊ ችግሮች ዙሪያ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት አወያይቷል፡፡

በመርሀግብሩ የኢንዱስትሪ ባለሙያዎች፣ በዘርፉ የተሰማሩ የፋብሪካ ባለሀብቶች፣ከብሔራ ንግድ ባንክ፣ከአካባቢጥበቃ ባለስልጣንና ከገቢዎች ሚኒስቴር የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈውበታል፡፡

በነበረው ውይይት አሁን ላይ በጥናት ከተለዩ ዋነኛ የዘርፉ ማነቆዎች መካከል የመሰረተ ልማትና የግብአት አቅርቦት፣ቴክኖሎጅን የመጠቀም አቅም፣ከአካባቢ ብክለት ጋር የተያያዙ ማህበራዊ ችግሮች፣የብድር አቅርቦት፣የገበያ ትስስር፣የምርት ትውውቅና ተቋማዊ ድጋፍ አለመኖር እንደዋና ተግዳሮቶች ተጠቅሰዋል፡፡

የውይይት መድረኩን የመሩት የኢፌድሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚንስትር ክቡር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው ችግሮቹ በአጭር ጊዜ የተከሰቱ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ ሲንከባለሉ የቆዩና ውስብስብ መሆናቸውን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከግብርና ሚኒስቴር፣ከአካባቢጥበቃ ባለስልጣን፣ከኢትዮ ቴሌኮም፣ከብሔራዊ ንግድ ባንክና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ለመስራት ከመቀናጀቱ በተጨማሪ ችግሮችን በሂደት ለመፍታት የቆዳ ልማት ስትራቴጅ ነድፎ ወደስራ መግባቱን ከአብራሩ በኋላ በቀጣይ መፈፀም ያለባቸውን ተግባራት አስመልክቶ የሚከተሉትን አቅጣጫዎች ሰጥተዋል፡፡

1.የኢንዱስትሪው ባለቤቶች ጥራት ያለው ቆዳ ለሚያቀርቡ ገበሬዎች አበረታች ዋጋ የሚከፈልበትን ስልት መቀየስ አለባቸው፡፡

2.ለአምራች ኢንዱስትሪው መንግስት የመሰረተ ልማትና ብድር አቅረትቦት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ስለሚሰራ ፋብሪካዎች ብድር ለማግኘት መጀመሪያማሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች አሟልተው መገኘት አለባቸው፡፡

3.የዘርፉን ችግሮች በጥናት ለይቶ የሚያቀርብና ተከታትሎ እንዲፈቱ የሚተጋ ጠንካራ የዘርፍ ማህበር ሊመሰረት ይገባል፡፡

4.እያንዳንዱ ፋብሪካ በውስጡ ያለውን አስተዳደራዊና መዋቅራዊ ችግር መፍታት አለበት፡፡

5.ፋብሪካዎች ከካይዘን አኳያ ያለባቸውን ክፍተት መቅረፍ አለባቸው፡፡

6. ፋብሪካዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከዲዛይን ጋር ተያይዞ ያሉ አሰራሮችን መቀየርና ማሻሻል አለባቸው፡፡

7. ገበያን በተመለከተ የውስጥ አቅምን ለመጠቀም የትምህርት ቤቶች ጫማ እንደ ልብስ ዩኒፎርም የሚሆንበት አሰራር እንዲተገበር ሚኒስቴር መስሪያቤቱ እየተንቀሳቀሰ ስለሆነ የጫማ ፋብሪካዎች የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ መስራት አለባቸው፡፡

8. የግብአት አቅርቦትን ችግር ለመቅረፍ ፋብሪካዎች በቀጥታ ከገበሬዎች የሚገዙበትን አሰራር መዘርጋት አለባቸው፡፡

9.የኮንትሮ ባንድ ንግድ በተዘዋዋሪ መንገድ የሀገር ውስጥ ፋብሪካዎችን ስለሚጎዳ ባለድርሻ አካላት በድርጊቱ አለመሳተፍ ብቻ ሳይሆን ወንጀሉን ተከታትሎ ከመታገል አንፃር የራሳቸውን ጉልህ ሚና መጫወት አለባቸው፡፡

ይከታተሉን

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post