የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በመሰማራት ለሀገር ኢኮኖሚ ማደግ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይጠበቅባቸዋል(ክቡር አቶ ሀሰን መሐመድ)

መጋቢት 5/2016 ዓ.ም (ኢሚ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት በዘርፉ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ መልካም አጋጣሚዎችና ማበረታቻዎችን ለሀገር ውስጥ ባለሀብቱ በማስተዋወቅ ለዘርፉ ዕድገት የሚያበረክተውን ተሳትፎና ሚና ለማሳደግ ዓላማው ያደረገ የአምራች ኢንዱስትሪ የኢንቨስትመንት የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የግብዓትና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሀሰን መሐመድ በውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ በአጠቃላይ በአገራችን የኢኮኖሚ ዕድገትና ሽግግር ውስጥ ያለውን ድርሻ ለማሳደግ የሀገር ውስጥ ባለሀብቱ ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ ወደ አምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በመሰማራት በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል።

በተቀናጀ እና በተናበበ አመራር የአምራች ኢንዱስትሪውን ማነቆዎች በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ሃገራዊ ሥርዓት በመዘርጋት እና የኢንዱስትሪያል ማህበረሰብ እንዲፈጠር በማድረግ አምራች ኢንዱስትሪው ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ስኬትና በልማት እቅዱ የታለመውን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲወጣ ለማስቻል “ኢትዮጵያ ታምርት” ሀገራዊ ንቅናቄ ወደ ተግባር ገብቶ በርካታ ለውጦችና ስኬቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ገልፀዋል።

በውይይቱ የሀገራችንን የአምራች ኢንዱስትሪ ታሪካዊ ዳራና አሁናዊ የዘርፉ የኢንቨስትመንት አማራጮች፣መልካም አጋጣሚዎችና የማበረታቻ ስርዓቶችን የሚያሳይ ሰነድ እየቀረበ ነው።

ይከታተሉን

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post