የአምራቾችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የመንግስትና የግል ዘርፍ የጋራ ምክክር ወሳኝነት አለው (የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚ/ዴኤታ አቶ ሀሰን ሙሐመድ)

መጋቢት 9/2016 ዓ.ም (ኢሚ) በኢትዮጵያ የዱቄትና የዱቄት ውጤቶች አምራቾች ዘርፍ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች እና መፍትሄ አቅጣጫ ላይ ያተኮረ የመንግስትና የግል ዘርፍ የጋራ ምክከር መድረክ ተካሄደ፡፡

በኢትዮጵያ ዱቄትና የዱቄት ውጤቶች አምራቾች ማህበር እና የጀርመን የልማት ትብብር (GIZ) ጥምረት በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ በአገራችን ብሔራዊ የጥራት እቅድ የተለየ ትኩረት ከተሰጣቸው የኢኮኖሚ መስኮች አንዱ የአምራች ኢንዱስትሪው የልማት ዘርፍ አንዱ ነው ያሉት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሃሰን ሙሐመድ ዘርፉ በጠቅላላ ሀገራዊ የምርት እድገት ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ የአገራችን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት ከፍተኛ ሚና መጫወት ይጠበቅበታል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የአምራቾችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የመንግስትና የግል ዘርፍ የጋራ ምክክር ወሳኝነት አለው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው የዱቄትና እና አኩሪ አተርን በመጠቀም የምግብ ዘይትን የሚያመርቱ የዘይት አምራቾች ያለባቸውን ችግር ከመንግስት፣ ከግሉ ዘርፍና ከሚመለከታቸው የልማት ድርጅቶች ጋር በጋራ ተወያይቶ በመፍታት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እና ለአገር ኢኮኖሚያዊ እድገት በጋራ መቆም ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በውይይቱም የስንዴና የአኩሪ አተር ማቀነባበሪያ አምራች ኢንዱትሪ ዘርፍ ላይ ያተኮረ የጥናት ሰነድ የቀረበ ሲሆን የመስሪያ ካፒታል፣ የምርት ጥራት ችግሮች፣ የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ ፣ የተጨማሪ የታክስ ሁኔታዎች መኖር ፣ ከማምረት አቅም አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ዘርፉን እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች እንደሆኑ ጥናቱ አመላክቷል፡፡

ይከታተሉን

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post