በአቶ መላኩ አለበል የተመራ የሱፐርቪዥን ቡድን በሠመራ የሚገኙ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትንና የኢንዱስትሪዎችን የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

መጋቢት11/2016ዓ.ም(ኢ.ሚ) በሠመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ያለውን የነዋሪዎች የመልማት ፍላጎት ሊያሳካ የሚችል የገቢ አሰባሰብና መሠረተ ልማት መሠራት አንዳለበት የኢንዱስትሪ ሚኒስትርና የሱፐርቪዥን ቡድኑ መሪ አቶ መላኩ አለበል ገለፁ።

በተቋማት መካከል ያለው ግንኙነት እየተጠናከረ ከሄደ ሰፊ የስራ ዕድሎች የሚፈጠሩበትና የተሻለ ገቢ የሚሰበሰብበት እንዲሁም የከተማው የመልማት ዕድል የሚጠናከርበት ነው ብለዋል።

ይሁንና እየተስተዋሉ ያሉ ክፍተቶችን በመሙላትና ጥንካሬዎችን በማስቀጠል ለተሻለ ውጤት ተግቶ መስራት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

በከተማ አስተዳደሩ ከሁሉም በተሻለ የሠላምና ፀጥታ ሁኔታው የተረጋገጠ መሆኑን የጠቀሱት አቶ መላኩ፤ ይህ ለሌሎች አካባቢዎች በተሞክሮነት ሊነሳ እንደሚችል ጠቁመዋል።

ከጤና መድህን አገልግሎት ጋር ተያይዞ በአጭር ጊዜ የተሰራው ስራ በበጎነት የሚነሳ መሆኑን ገልፀው፤ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሳካት ተቋማት ተናበው መሥራት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።

ከከተማ መሬት ፋይል አያያዝ፣ ከገቢ አሰባሰብ ጋር ጥሩ ጅምሮች መኖራቸውን ተናግረው እነዚህን ማጠናከር አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ይሁንና የህብረተሰብ የመልማት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚጨምር በመሆኑ ይህንን ሊያሳካ የሚችል የገቢ ማሰባሰብና የመሠረተ ልማት ስራ መሠራት አንደሚኖርበት ጠቁመዋል።

በከተማዋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተገነቡ የሚገኙትና አገልግሎት መሥጠት የጀመሩት ፋብሪካዎች ተስፋ ያላቸው ጭምር መሆኑንም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከኤሌክትሪክ ሐይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ጥያቄዎች ከሚመለከተው አካል ጋር ለመፍትሔው እንደሚነጋገሩም ጠቁመዋል።

የሱፐርቪዥን ቡድኑ በከተማዋ ተዘዋውሮ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን፣ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን፣ የጨውና የከረጢት ፋብሪካዎችን ተመልክቷል።

ይከታተሉን

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post