ያለሴቶች ተሳትፎ ቀጣይነት እና ውጤታማ ስራ መስራት ስለማይቻል ሴቶችን ማብቃት ያስፈልጋል

መጋቢት 20/2016 ዓ.ም (ኢ.ሚ) የኢፌደሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በዓለማቀፍ ደረጃ ለ113ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ48ኛ ጊዜ ሴቶችን እናብቃ ልማትና ሰላምን እናረጋግጥ በሚል መሪ ቃል የሴቶች ቀን አከበረ።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሴቶችና ማህበራዊ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ እየሩሳሌም ዳምጤ ያለሴቶች ተሳትፎ ቀጣይነት እና ውጤታማ ስራ መስራት ስለማይቻል ሴቶችን በማብቃት በኢኮኖሚ ዕድገት፣በፓለቲካ ተሳትፎ እና በማህበራዊ መስተጋብር መሻሻል የበኩላችንን ድርሻ መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ሰላም ለሴቶችና አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ እና ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት መሻሻል ከምንም በላይ ወሳኝ ነገር በመሆኑ በምንሰራው ስራ በምንሄድበት ሁሉ ለሰላም መረጋገጥ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ የዕለት ከዕለት ተግባራችን ልናደርገው ይገባልም ብለዎል ።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ እሸቱ ስጦታው ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሴቶችን አቅም ለማሻሻል ረጅምና አጭር ጊዜ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግና የገቢ መጠናቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሴት ሰራተኞችን ተደራጅተው የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎችን በትርፍ ጊዜያቸው እንዲሰሩና የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ ስለመሆኑም ገልፀዋል ።

የዕድገትና ተወዳዳሪነት ሚኒስትር ዴኤታው አማካሪ አቶ ዱጋሳ ዱንፋ በበኩላቸው የሴቶችን ቀን ማክበር ሴቶችን ከማብቃትና የሥርዓተ- እኩልነት ከማሻሻል አኳያ የሚኖረው ሚና ጉልህ መሆኑን ጠቅሰዉ ሴቶች ከድህነት እንዲወጡና በልማቱ ሁለንተናዊ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ ያለዉ ሥራ አበረታች ነዉ ብለዎል።

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post