የዓለም ባንክ ም/ፕሬዝደንት ሊሳ ሮሰን በአዲስ አበባ የሚገኙ አምራች ኢንተርፕራይዞችን ጎበኙ

መጋቢት 24/2016 ዓ.ም (ኢሚ) የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የግብዓትና መሰረተ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሀሰን መሐመድ፣ የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዘዳንት፣ የዓለም ባንክ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በዓለም ባንክ እየተደገፉ ያሉ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን የስራ ሁኔታ ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኙቱ የፕላስቲክ ገመዶችን የሚያመርተው አሁን ኢንጂነሪንግና ኤቲኤም ጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራች ኢንተርፕራይዞች የስራ ሁኔታ ተጎብኝቷል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በጉብኝቱ ወቅት እንደገለፁት የጉብኝቱ ዓለማ ከዓለም ባንክ ብድር አግኝተው በአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች በመሰማራት የስራ እድል የፈጠሩ እና በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ውጤታማነት በመመልከት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ለማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዘርፉ ትኩረት እንዲያገኝ ያደረገ ንቅናቄ ነው ያሉት ሚኒስትሩ በዘርፉ የሚታዩ የመስሪያ ካፒታል፣ የመስሪያ ቦታ፣ የገበያ ትስስር ችግሮችን በመፍታት ተዘግተው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲመለሱ፣ ዜጎች ወደ ስራ ገበታቸው እንዲቀጥሉ ና አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ዘርፉ እንዲሰማሩ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው ብለዋል፡፡

የዓለም ባንክ ቡድን ምክትል ፕሬዘዳንት ሊሳ ሮሰን በበኩላቸው በጉብኝታቸው ባዩዋቸው እንቅስቃሴዎች መደሰታቸውን ገልጸው የተመለከቷቸው አምራች ኢንዱስትሪዎች ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተጣጣመ ስራ እየሰሩ መሆኑ ስራቸው ከዓለም ባንክ ዓላማ ጋር የተሳሰረ መሆኑን በመጥቀስ በቀጣይም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ በትብብር እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራዝ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለባቸው ንጉሴ በበኩላቸው የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች የፋይናንስ ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ስምምነት ከዓለም ባንክ ጋር በማካሄድ ላለፉት አምስት ዓመታት ለአምራቶች የመስሪያ ማሽንና የስራ ማስኬጃ ያለምንም ማስያዣ በማቅረብ ውጤታማ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post