የግድቡ መጠናቀቅ በኃይል እጥረት ወደኋላ የቀሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲያንሰራሩ ያደርጋል” (አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ)

መጋቢት 25/2016 ዓ.ም (ኢ.ሚ) የዓባይ ግድብ መጠናቀቅ በኃይል አቅርቦት ላይ ያለውን ችግር በመፍታት ወደኋላ የቀሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲያንሰራሩና እንዲጠናከሩ እንደሚያደርግ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀⵆ

የኃይል አቅርቦት ውስንነት ከፍተኛ የሰው ኃይል መያዝ የሚችሉ ኢንዱስትሪዎች የሥራ ዕድል እንዳይፈጥሩ ሲያደርግ መቆየቱም ተገልጿል፡፡

አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ለኢፕድ እንደገለጹት፣ አምራች ኢንዱስትሪው ተግዳሮቶቹ የተለያዩ ቢሆኑም በቂ የሆነ የኃይል አቅርቦት አለመኖር፣ የኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል፡፡ እነዚህ ችግሮች ደግሞ ኢንዱስትሪዎቹ በበቂ ሁኔታ ማምረት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል፤ አሁን ላይ የግድቡ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረስ ግን ችግሮቹን ለመፍታት ትልቅ አቅም ነው፡፡

በቂና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ቢያገኙ የማስፋፋት ሥራ በመሥራት ምርታቸውን በእጥፍ ለማሳደግ የተዘጋጁ አምራች ኢንዱስትሪዎች አሉ ያሉት አቶ ታረቀኝ፤ የኃይል አቅርቦት ውስንነት ከፍተኛ የሰው ኃይል መያዝ የሚችሉ ኢንዱስትሪዎች የሥራ ዕድል እንዳይፈጥሩ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል፡፡

የዓባይ ግድብ መጠናቀቅ በኃይል አቅርቦት ላይ ያለውን ችግር ፈትቶ ወደኋላ የቀሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲያንሰራሩና እንዲጠናከሩ፣ ተጨማሪ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

“ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ የአምራችነት ደረጃ ላይ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ይፈልጋሉ፡፡ ከፍተኛ ኃይል ከመጠቀም አንጻር ለምሳሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ እራሱን የቻለ ኃይል ያስፈልገዋል፡፡ ይህ መሆኑ ረዘም ያለ የሥራ ጊዜ እንዲኖራቸው ያስችላል” ብለዋል፡፡

እንደ ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ያሉት ደግሞ በትልልቅ አምራች ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚመደቡ በመሆናቸው ከፍተኛ ኃይል ይጠቀማሉ የሚሉት አቶ ታረቀኝ፤ የኃይል አቅርቦት ምቹ ሲሆን፣ በተጨማሪ ትላልቅ የሚባሉ ኢንዱስትሪዎች እየመጡ መሆኑንም አብራርተዋልⵆ

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post