"የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን ለመገንባት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ውጤት እያመጣ ነው" (አቶ መላኩ አለበል)

መጋቢት 30/2016ዓ.ም (ኢ.ሚ) ዶዳይ ማኑፋክቸሪንግ ያመረታቸውን የኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክሎች አስመረቀ።

በምረቃው መድረክ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ እንደገለፁት የኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክሎቹ እንደሀገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ትልቅ ሚና አላቸው።

አቶ መላኩ አለበል አያይዘውም ይህ ዘርፍ ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር፣ የአካባቢን ደህንነትን በማስጠበቅ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማስፋት ብሎም እንደ ሀገር ያሉብንን የሎጅስቲክ ችግሮች በመቅረፍ የዜጎችን የኑሮ ጫና ይቀንሳል ሲሉ ገልፀዋል።

ላለፉት አመታት የአምራች ኢንዱስትሪው እና አጠቃላይ ኢንቨስትመንቱ እየተነቃቃ ነው ያሉት አቶ መላኩ ይህንንም የሚያግዝ የንግድ ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ፣ የፋይናንስና የውጪ ምንዛሬ አቅርቦት የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

እንደ ሀገር የአረንጓዴ ኢነርጂ ለማምጣት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ውጤት እያመጣ ቢሆንም ለነዳጅ ምርት ከምናወጣው አንጻር ዋጋ እያስከፈለን ነው ይህንንም ለመቅረፍ በኤሌክትሪክ በተሽከርካሪዎች ላይ አትኩረን ልንሰራ ይገባልም ብለዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሂሮኖሪ ሺባቲ በበኩላቸው ዶዳይ ማኑፋክቸሪንግ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረጉ ለሌሎች የጃፓን ባለሃብቶች በር ከመክፈቱም በተጨማሪ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ትስስር የማጠናከር አቅም አለው ሲሉ ገልፀዋል።

Share this Post