የግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ወደ ውጭ በመላክ የአምራች ኢንዱስትሪውን ገበያ ድርሻ ለማሳደግ እየተሰራ ነው (አቶ ሐሰን ሙሐመድ)

አዲስ አበባ 04/08/2016 ዓ.ም (ኢ.ሚ) የተቀናጁ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች አሠራርና ዘላቂነት በኢትዮጵያ ፕሮጀክት ላይ ትኩረት ያደረገ የፌደራል፣ክልል ከፍተኛ አመራሮች እና የልማት አጋሮች የተገኙበት ውይይት ተካሄደ፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የግብዓትና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሐሰን ሙሐመድ መንግስት የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ተግባር በመገንዘብ ለአራቱ ፓይለት ትግበራዎች ድጋፍ የሚሆኑ በርካታ የልማት አጋሮችን እና የገንዘብ ድጋፍ ዘዴዎችን በማሰባሰብ እየሰራ ነው ብለዋል።

የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ለኢትዮጵያ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ የላቀ ሚና አለው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው የግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ደረጃውን የጠበቀ ጥራት ያለው ምርት ወደ ውጭ በመላክ የአምራች ኢንዱስትሪውን ገበያ ድርሻ ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል ።

የተቀናጁ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ15ሺ600 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል የፈጠሩ ሲሆን ከ140ሺ000 አነስተኛ አርሶ አደሮች ጋር በተፈጠረው የወጪ ንግድና አቅርቦት ሰንሰለት ትስስር በተለይም በይርጋለም፣ ቡሬ እና ቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መፈጠሩን ገልፀዋል ።

ለተቀናጁ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች አሠራርና ዘላቂነት በኢትዮጵያ ፕሮጀክት ከጣሊያን መንግስት 22 ሚሊየን ዩሮ ብድር መገኘቱን አስታውሰው ።

የተገኘው ገንዘብ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት በኩል በፓርኩ እና በአካባቢው ላሉ አግሮ ፕሮሰሰሮች የብድር መስመር አገልግሎት እንደሚሰጥ እና የምርት ጥራት መቆጣጠሪያ ላብራቶሪ ግንባታ ድጋፋ እንደሚውል ተናግረዋል ።

የተካሄደው የውይይት መድረክ የተቀናጁ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች አሠራርና ዘላቂነት በኢትዮጵያ ፕሮጀክት የመጀመሪያው የፌዴራል ፕሮጀክት አስተባባሪ ኮሚቴ ነው፡፡

#ኢትዮጵያ_ታምርት #እኛም_እንሸምት

Share this Post