የማሽነሪ አምራች ኢንዱስትሪ ኢኮኖሚያዊ ሽግግሩን ውጤታማ ከማድረግ በተጨማሪ ለዜጎች የስራ ዕድል ፈጠራ ዓይነተኛ ሚና አለው ተባለ፡፡

ሚያዚያ7/2016 ዓ.ም የዘርፉን ችግር መፍታት ዓላማው ያደረገ የማሽነሪ አምራች ኢንዱስትሪዎች ሀገራዊ ዕድሎችና ተግዳሮቶች ላይ ያተኮረ ልዩ የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡

በዕለቱ የውይይት መድረኩን የመሩት ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል የማሽነሪው ኢንዱስትሪ የግብርናውን ምርታማነትና ሀገር አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ሽግግሩን ውጤታማ ከማድረግ ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ የላቀ ድርሻ እንዳለው ገልፀዋል፡፡

በምክክር መድረኩ የ10 ዓመቱ የኢንዱስትሪ ልማት ዕቅድ፣በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች፣በሀገሪቱ ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ነባራዊ ሁኔታና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ተብራርተዋል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ተቀርጾ ወደ ስራ መገባቱ፣ በርካታ የኢንዱስትሪ ስትራቴጅዎች መቀረፃቸው፣መንግስት በሚያካሂዳቸው ግዥዎች ለሀገር ውስጥ አምራቾች ቅድሚያ መሰጠቱ ለዘርፉ የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች መሆናቸውን ሚኒስትሩ ገልጸው የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር፣የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ለፋብሪካዎች የሚሰጠው የብድር አቅርቦት በቂ አለመሆኑ፣በገዥዎች በኩል ሀገር ውስጥ ምርቶችን የመግዛት ልምድ ዝቅተኛ መሆን፣በጥራትና በአነስተኛ ወጭ ማምረት የሚያስችሉ ቴክኖሎጅዎችን የመጠቀም ልምድ እንደ ችግር ተጠቅሰዋል፡፡

በፌደራል ደረጃ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት አስተባባሪ ኮሚቴ መቋቋሙን ያስረዱት ሚኒስትሩ ለማሽነሪ አምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ በመቀረጽ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዘርፉንም ለማሳደግ የማበረታቻ ስርዓት እንደ ሚዘጋጅ አክለው ችግሮቹን ለመፍታት በሁሉም ክልሎች የማሽነሪ አምራቾች ማህበር መቋቋም እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በመርሀ -ግብሩ ከማሽነሪ ኢንዱስትሪ ባለቤቶች በተጨማሪ የሚመለከታቸው ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

#ኢትዮጵያ_ታምርት #እኛም_እንሸምት

Share this Post