የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ማነቆዎች በመፍታት ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው(ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ )

አዲስ አበባ ግንቦት 05/2016(ኢሚ) ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ውስን እንዲሆን አድርገው የቆዩ ችግሮችን በመለየት ደረጃ በደረጃ እየተፈቱ መሆኑን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥሟቸውን ማነቆዎች በመፍታትና የመልማት እድሎችን በመጠቀም ስኬቶች የተመዘገቡበት መሆኑን አቶ ተመስገን ገልፀዋል ።

የኢትዮጵያ ታምርት ዓላማ ዘርፉ በሚፈለገው ልክ እንዳያድግ ያደረጉ ችግሮችን መለየት እና የልማት እድሎችን መጠቀም መሆኑንም የገለፁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንቅናቄው አምራች ኢንዱስትሪው ከየት ተነስቶ የት መድረስ እንዳለበት ከማመላከት ባለፈ ተኪ ምርቶችን በማምረት ተጨባጭ ለውጥ እንዲመዘገብ አስችሏል ብለዋል።

መንግስት ለጀመረው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር መሰረት የሚሆኑ ውጤቶች በአምራች ዘርፉ እየተመዘገቡ መሆኑን የገለፁት አቶ ተመስገን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ዓላማውን ከግብ በማድረስ የተሳካ እንደነበር ጠቅሰዋል።

በአምራች ኢንዱስትሪዎች ዘንድ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ጸጋ በአግባቡ ለመጠቀም የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ለአምራቾች ዘላቂ የገበያ ትስስር መፍጠርና በሀገር ወስጥ ምርት የመኩራት እሴትን በዘላቂነት መገንባት የሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ቀጣይ የቤት ስራ መሆን አለበት ያሉት አቶ ተመስገን በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የመንግስት ተቋማት የሀገር ውስጥ አምራቾችን ምርት እንዲጠቀሙ የማድረግ ስትራቴጂ ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልፀዋል ።

Share this Post