የመላው ኢትዮጵያውያንን የሀገርን ምርት የመጠቀም ባሕል ማሳደግ ያስፈልጋል(ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ)

ግንቦት 06/2016 ዓ.ም (ኢ.ሚ) የመላው ኢትዮጵያውያንን የሀገርን ምርት የመጠቀም ባሕል ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናግረዎል።

"ኢትዮጵያ ታምርት ደግሞም ትጠቀም!" ሲሉ የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዓላማው ሁለት ነው ብለዋል። የመጀመሪያው እንደ ሀገር ያሉንን የልማት ዕድሎች እጅግ በተሻለ መንገድ መጠቀም ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ዘርፉ በሚፈለገው ልክ እንዳያድግ ያደረጉ ማነቆዎችን በቅንጅት ለመፍታት ለማገዝ እንደሆነ ገልፀዎል።

መንግሥት ለዘርፉ እድገት ልዩ ትኩረት በመስጠት ኢትዮጵያ እንድታመርት ብቻ ሳይሆን ያመረተችውን እንድትጠቀምም በትልቅ ትኩረት እየሠራ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ "መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም የሀገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ባሕልን እንዲያጎለብት ጥሪ እናቀርባለን" ሲሉም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ መልእክታቸውን አስፍረዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትላንት ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ማጠናቀቂያ ሥነ ሥርዓት ላይ መታደማቸውን ገልጸዋል።

Share this Post