አምራች ኢንዱስትሪዎች የአስተዳደርና የባለሙያ ክህሎት ችግራቸውን በጥናት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ መስጠት መቻል አለባቸው

ግንቦት 21/2016 ዓ.ም (ኢሚ) የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር በመተባበር ባሰናዳው የመንግስትና የግል ዘርፉ የውይይት መድረክ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ሚኒስትሩ አቶ መላኩ የትኛውም አምራች ኢንዱስትሪ ከመንግስት የሚፈልገው የፋይናንስ ፍላጎት ቢቀርብለትና ሁሉም መሠረተ ልማት ቢሟላለት የውስጥ የአስተዳደር ሂደቱን ዘርፉ የሚጠይቀውን ዕውቀትና የዘመኑን ቴክኖሎጅ በዋጁ አመራሮች በመመራት የሰራተኞቹን የክህሎት ክፍተት ተከታታይነት ባለው የስራ ላይ ስልጠና በመፍታት መስራት እስካልቻለ ድረስ ዘርፉ የሚፈለገውን ተቋማዊና ሀገራዊ ዕድገት ማስመዝገብ አይችልም።

ሚኒስትሩ አክለውም መንግስት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የጋራ ምክር ቤት(ማህበር) መቋቋም አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልፀው አምራቾች ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች በተባበረ ክንድ መፍትሄ ለመስጠትና ከአቅማቸው በላይ ለሚሆኑ ቸግሮች ለመንግስት ጥያቄና የፖሊሲ አማራጮችን ለማቅረብ ጉልህ ሚና ለሚኖረው የጋራ ተቋማቸው የዘርፍ ማህበሩ ዕውን መሆን በጋራና በመሰባሰብ በትጋት እንዲሰሩ አሳስበዋል ።

የሀገርን ኢኮኖሚያዊ በማይናጋ መሠረት ላይ በመጣል ዘላቂ ኢኮኖሚ መገንባት የሚቻለው በአምራች ዘርፉ በመሆኑ መንግስት ከመቼውም ጊዜ በላይ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ ከትናንት ዛሬ ከዛሬ ነገ የተሻለ ጥራትና ተፈላጊነት ያለው ምርት በብዛት ማምረት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በውይይት መድረኩ የአምራች ዘርፉን አሁናዊ አጠቃላይ ቁመና የሚያሳይ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

Share this Post