የኬሚካል ውጤቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል ውይይት ተካሄደ

የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከግብጽ የጸረ ተባይና ኬሚካል አምራች ድርጅት ተወካዮች ጋር በአገር ውስጥ የክሎሮ አልካሊ ውጤቶችን ለማምረት በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ተወያይቷል፡፡

በኢትዮጵያ ለአምራች ኢንዱስትሪው መደላድል የሚፈጥሩ በርካታ ሁኔታዎች አሉ ያሉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሐሰን ሙሃመድ ሰፊ የገበያ እድል፣ ከፍተኛ አምራች የሰው ኃይል መኖር፣ የተቀናጁ አግሮ ኢንዱስትሪና ኢንዱስትሪ ፓርኮች መኖር ፣የተመረጡ የኢኮኖሚ ዞኖች መገንባታቸው እና እንደ አፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጠና እና ሌሎች የንግድ ስምምነቶችን ለአብነት በምቹ ሁኔታነት አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት መስጠቱንና የጠቆሙት አቶ ሀሰን በዘርፉ ኢኮኖሚያዊ መወቅራዊ ሽግግር ለማምጣትም ከአደረጃጀት ጀምሮ አስፈላጊ የህግ ማዕከቀፎችን የማዘጋጀትና የማስተካከል ፣የአስር አመት የልማት ዕቅድ እንዲሁም አገር በቀል የአኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሞች ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ጸረ ተባይ ማጥፊያ፣ ማዳበሪያ እና መሰል የኬሚካል ውጤቶችን ወደ ሀገር ውስጥ እንደምታስገባ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው እንደ አገር ዘርፉ ሰፊ ፍላጎት የሚታይበትና ያልተነካ እንደመሆኑ አምራች ድርጅቶቹ በኬሚካልና ኬሚካል ውጤቶች ዘርፍ ቢሰማሩ ውጤታማ እና ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል፡፡

በውይይቱም ከፍተኛ ፍላጎት የሚታይበትን የክሎሮ አልካሊ ውጤቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል የጥናት ሰነድ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብአቶች ኢንዱስትሪ ምርምር ልማት ማዕከል ስራ አስፈጻሚ በሆኑት አቶ ሃብታሙ አራጌ ለውይይት ቀርቧል፡፡

Share this Post