በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው ኢንተርፕራይዞች ማገገሚያ ፕሮጀክት ተጀመረ

ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (ኢ.ሚ) ከአውሮፓ ኅብረት፣ ከጀርመንና ከኔዘርላንድስ መንግሥታት በተገኘ ድጋፍ፣ በሰሜን ጦርነት ቀጥተኛ ተጎጂ በሆኑት በአፋር፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች የሚገኙ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን መልሶ ማቋቋም ላይ ያተኮረ የአራት ዓመት ፕሮግራም ተጀመረ።

በሦስቱ አካላት የጋራ ፈንድ የተጀመረው ፕሮግራም ከኅብረቱ ጋር በቅርበት ከሚሠራ አንድ የልማት ባንክ፣ አንድ ዓለም አቀፍ የጀርመን ልማት ድርጅትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የካፒታል ልማት ፈንድ (ዩኤንሲዲኤፍ) በኩል ተግባራዊ የሚደረግ ነው ተብሏል፡፡

ፕሮግራሙን የሚያስፈጽሙት አካላት ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ የመንግሥት ተቋማት ጋር በጋራ እንደሚሠሩ የተገለጸ ሲሆን፣ የድጋፍ ስምምነቱን ከኢትዮጵያ በኩል የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ሀሰን መሀመድ ፈርመዋል።

በአጠቃላይ ኢኮኖሚውንና በውስን ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን መልሶ የማቋቋም ሥራ በግጭት ለተጎዱ አካባቢዎች የሚያስፈልጉ የሥራ ቅጥርና ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን መልሶ ለማስፋፋት ሥራ ራሱን የቻለ የተለየ አካሄድ ሊበጅለት የሚገባ መሆኑን ማሳያ እንደሆነ፣ የአውሮፓ ኅብረት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አሳውቋል።

ጂአይዜድ የተባለው የጀርመን መንግሥት የልማት ዓላማዎችን ለማሳካት የሚሠራ ዓለም አቀፍ ተቋም ደግሞ ኢንተርፕራይዞቹ በፍጥነትና በጠንካራ ሁኔታ ማገገም እንዲችሉ፣ እንዲሁም ለብድር ብቁ የመሆን አቅማቸውን በማሳደግ የፋይናንስ ተጠቃሚነታቸውን ከፍ እንዲያደርጉ የሚያግዝ ቀጥተኛ የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያቀርብላቸው ተነግሯል።

ዓለም አቀፉ ተቋም ከዚህም ባሻገር በኢንተርፕራይዞቹና በአበዳሪ ገንዘብ ተቋማት መካከል ጥሩ የሥራ ግንኙነት ሊኖራቸው የሚችለውን እየለየ እንደሚያገናኝም ተነግሯል።

ምንጭ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ

Share this Post