ኢትዮጵያ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከቻይና ጋር አብራ የምትሰራባቸው በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳሏት ተገለጸ፡፡
ሰኔ1/2016 ዓ.ም የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ልዑካን ከኢፌድሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በተመለከተ ተወያይተዋል፡፡
የቻይና መንግስት ልዑካንን ተቀብለው ያወያዩት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚንስትር ደኤታ ክቡር አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ኢትዮጵያና ቻይና አያሌ ዓመታትን ያስቆጠረ ጤናማ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው ካብራሩ በኋላ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ቻይና ኢትዮጵያ ውስጥ መስራት የምትችልባቸው ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
የውይይቱ ዋና ዓላማ በሀገረ ቻይና በጋንዞዩ (Ganzhou) ክልል የሚገኙ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ መጥተው በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚሰማሩበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡በነበረው መርሀ ግብር አቶ ታረቀኝ ኢንቨስትመንትና ንግድ የኢትዮ ቻይና የዲፕሎማሲ ትኩረት መሆኑን ጠቅሰው በዘርፉ ሀገሪቱ ውስጥ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለልዑካኑ አስረድተዋል፡፡
የቻይና ልዑካንም በበኩላቸው ኢትዮጵያዊ ውስጥ ለሚመረቱ ምርቶች በሀገራቸው ያሉ የገበያ አማራጮችን አሳይተዋል፡፡በተጨማሪም ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ በትብብር ለመስራት በከፍተኛ ደረጃ አዲስ መነቃቃትንና ምቹ ሁኔታን ፈጥሮልናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡