ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በሀገር ውስጥ ለሳፋሪ አገልግሎት ተሽከርካሪነት የተቀየሩ ባለአንድ ጋቢና ፒክ አፕ መኪናዎችን በናሙናነት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስረክቧል።

ሰኔ 6/2016 (አ.ሚ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በሀገር ውስጥ ለሳፋሪ አገልግሎት ተሽከርካሪነት የተቀየሩ ባለአንድ ጋቢና ፒክ አፕ መኪናዎችን በናሙናነት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስረክቧል።

ቱሪዝም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም ቅድሚያ ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ በመሆኑ ልማትን እና አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል ብሎም በዘርፉ ልምድን ማዳበር ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ብዛት ያላቸው ብሔራዊ ፓርኮች እና የዱር እንስሳት ሃብት ባላት ኢትዮጵያ የሳፋሪ ልምምድን ማስፋፋት ቱሪስቶችን ለመሳብ ወሳኝ ተግባር መሆኑንም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በየካቲት 2016 የሚኒስትሮች ም/ቤት የ100 ቀናት ግምገማ ወቅት ለቱሪዝም አገልግሎት የሚሰጡ የሳፋሪ ተሽከርካሪዎች እንዲመረቱ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አቅጣጫ መስጠታቸው ይታወቃል፡፡

በዚህ መሰረትም ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በሀገር ውስጥ ለሳፋሪ አገልግሎት ተሽከርካሪነት የተቀየሩ ባለአንድ ጋቢና ፒክ አፕ መኪናዎችን በናሙናነት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስረክቧል።

መኪናዎቹን ለሳፋሪ አገልግሎት እንዲመቹ አድርጎ በመለወጥ ሒደት ውስጥ አምራቾች በሀገር ውስጥ በስፋት የመለወጥ ልምድ እና አቅም ለማዳበር መቻላቸው ተጠቅሷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት÷ በምርት ስራው የተሳተፉና አቅም ያላቸው አምራቾች የምርት ሥራውን ሒደት እንዲያስፋፉ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

Share this Post