የክልሉን እምቅ አቅም ወደ ምርት ለመቀየር እየተሰራ ነው
ህዳር 13/2017ዓ.ም (ኢሚ) ሀገራችን ከፍተኛ መጠን ያለው ኬሚካል ውጤቶች ከውጭ እያስገባች ትገኛለች፡፡ ከነዚህ ኬሚካሎች ውስጥ ብዙዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት እምቅ አቅም ቢኖርም እስካሁን ሳናመርት ቆይተናል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በአፋር ክልል አፍዴራ ሃይቅ የተመረተውን ጨው ወደ ክሎሮ አልካሊ ለመቀየር ጥናት አጥንቶ ለሚያለሙው ባለሃብቶች የማስተዋወቅ ስራ አከናውኗል፡፡
የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ሐጂ አወል አርባ ባለሃብቶች ጥናቶችን መነሻ በማድረግ በክልላችን የሚገኙ እምቅ ሃብቶችን ለማልማት ለሚመጡ ባለሃብቶች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የመሰረተ ልማትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሀመድ የሀገር ውስጥ ግብዓትን በመጠቀም መሰረታዊ ኬሚካልን በሀገር ውስጥ በማምረት የአምራች አንዱስትሪውን ተወዳዳሪነት ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡
አያይዘውም አዲሱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ይህን ምቹ ሁኔታ እንደሚደግፍ በመግለጽ ፖሊሲውን ለማስፈጸም የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡
የአፋር ክልል የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አይሻ ያሲን በበኩላቸው ክልሉ በብዙ ዘርፎች ኢንቨስት ለሚያደርጉ ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸት የክልሉን ኢንቨስትመንት እያሳደገ እንደሚገኝ ገልፀው በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሃብቶችን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡
የግል ባለሃብቶች መንግስት ወደ ዘርፉ እንድንገባ የሚያደርግልን ማበረታታት በሀገራችን የሚገኙ ፀጋዎች ላይ ኢንቨስት በማድረግ ራሳችንንም ሀገራችንንም ለማሳደግ ከፍተኛ ጥቅም አለው ብለዋል፡፡
ጥናቱን ሲያስተባብሩ የነበሩት በአምራች ኢንዱሰትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ስራ አስኪያጅ አቶ ሃብታሙ አራጌ ጨውን መነሻ አድረጎ የሚነሱ ብዛት ያላቸውን ክሎሮ አልካሊ ኬሚካል ክልሉ ከፍተኛ እምቅ ሃይል እንዳለው ጥናቱ አሳይቷል ብለዋል፡፡
#ኢትዮጵያ_ታምርት
#እኛም_እንሸምት