በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የ2016 ኤክስፖ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ተከናውኗል(ክቡር አቶ መላኩ አለበል)

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሰፊ የስራ ዕድል በመፍጠር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት፣ ጥራት ያለው ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ የሀገሪቱን ጥቅል ኢኮኖሚያዊ እድገት ድርሻ ለማሳደግ ያለመ ነው።

በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ንቅናቄውን በይፋ ካስጀመሩበት ከሚያዚያ/2014 ዓ.ም ጀምሮ ተዘግተው የነበሩ በርካታ አምራች ኢንዱስትዎች ወደ ስራ ገብተዋል።

ንቅናቄው ተኪ ምርቶችን ከማቅረብም ባለፈ ለውጭ ገበያ በማዘጋጀት በአምራች ዘርፉ ላይ መነቃቃት እንዲፈጠር አድርጓል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በኤክስፖው ማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኤክስፖው የተለያዩ ስኬቶች የተመዘገቡበት ነበር ብለዋል።

በኤክስፓው ከመቶ ሺህ በላይ ግለሰቦችና ተቋማት መሳተፋቸውን ገልጸው፣ ከ57 ሀገሮች የመጡ ድርጅቶች እንዲሁም 157 ዲፕሎማቶች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።

በአጠቃላይ 210 አምራች ኢንዱስትሪዎች የተሳተፉ ሲሆን 8ሺህ 188 አይነት ግብይት የተፈጸመ ሲሆን በገንዘብ ደረጃ ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት መከናወኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የ2017 ኤክስፖ ከሚያዚያ 30 እስከ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም ለሰባት ቀን እንዲካሄድ መወሰኑንም ጠቁመዋል።

ከግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ታምርት የ2016 ኤክስፖ ማጠቃለያ መርሐ ግብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የአምራች ኢንዱስትሪ ተወካዮች በተገኙበት እየተካሄደ ነው።

ኢትዮጵያ_ታምርት #እኛም_እንሸምት

Share this Post