በ2017 በጀት ዓመት የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የኤክስፖርት አቅም 8% አድጓል(አቶ መላኩ አለበል)

ሀምሌ 23/2017 ዓ.ም (ኢ.ሚ) የኢፌድሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ አመራሮችና በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈፃፀም ካላቸው ስልሳ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር የ2017 በጀት ዓመት የኤክስፖርት አፈፃፀምንና የ2018 በጀት ዓመትን የኤክስፖርት ዕቅድ አስመለክቶ የውይይት መድረክ አካሄደ፡፡

ውይይቱን የመሩት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚንስትር አቶ መላኩ አለበል በ2017 በጀት ዓመት በዘርፉ የነበረው ኤክስፖርት ከ2016 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ8% ዕድገት ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡

የውይይቱ ዓላማ የአምራች ኢንዱስትሪውን የኤክስፖርት አቅም ለማሳደግ በሚረዱ ጉዳዮች ላይ ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ነው ያሉት ሚኒስትሩ የኤክስፖርት አፈፃፀማችን ባለፉት ዓመታት ከነበረበት ደረጃ እየተሸሻለ ቢመጣም እንደ ሀገር ካለን አቅም አኳያ መድረስ የነበረበትን ደረጃ አለመድረሱን በመጥቀስ መንግስት የሚጠበቅበትን የመሰረተ ልማት ዝርጋታና የማበረታቻ ስርዓቶችን እስካሟላ ድረስ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚጠበቅባቸውን ውጤት ካላመጡ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስገንዝበዋል፡፡

የኤክስፖርት አቅም እንዲያድግ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ማነቆ ለመፍታት ብሔራዊ የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስሉ የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ሚንስትሩ የተፈጠረለትን ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ ሁሉም አምራች ኢንዱስትሪ የሚጠበቅበትን ውጤት የማምጣት ግዴታ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም አምራች ኢንዱስትሪዎች ከአስተዳደርና ከክህሎት ክፍተት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ በራሳቸው አቅም መፍታት፣ አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን ለመጠቀም መስራትና ችግሮችን ስር ሳይሰዱ በአጭሩ ለመፍታት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በየአስራ አምስት ቀኑ በሚያካሂደው የውይይት መድረክ ላይ መሳተፍ እንዳለባቸው አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post