በሀምሌ ወር ኤክስፖርት በተደረጉ ምርቶች 33 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተገኘ።

ነሀሴ 7/2017 ዓ.ም (ኢ.ሚ) የኢፌዲሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የ2018 በጀት ዓመት የሀምሌ ወር የአምራች ኢንዱስትሪዎች ኤክስፖርት አፈፃፀምን በተመለከተ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል፡፡

የግምገማ መድረኩን የመሩት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል አምራች ኢንዱስትሪዎች መንግስት በሚያደርገው ድጋፍ ልክ ውጤት እንደሚጠበቅባቸው ተገንዝበው እንደ ሀገር የተያዘውን የኤክስፖርት ዕቅድ ለማሳካት በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የሀምሌ ወር ዕቅዳቸውን ማሳካት ያልቻሉ በነሀሴ ወር አመርቂ ውጤት ማምጣት፣ እቅዳቸውን ያሳኩ አምራቾች ስኬታቸውን በላቀ ሁኔታ ማስቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በመርሀ ግብሩ በቀረበው ሪፖርት በሀምሌ ወር ኤክስፖርት በተደረጉ ምርቶች 33 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገልጿል ፡፡

በሀምሌ ወር የተለያዩ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ 37.5 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ከነበረው ሀገራዊ ዕቅድ አኳያ ሲታይ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያውን ወር የኤክስፖርት አፈፃፀም 94% ማሳካት ተችሏል ፡፡

አፈፃጸሙ ከ2017 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር ኤክስፖርቱ 43% ዕድገት እንዳለው ያሳያል፡፡

በውይይቱ በኤክስፖርት አቅማቸው የተመረጡ ስልሳ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ የዘርፉ ባለሙያዎችና የስራ ሀላፊዎች የተሳተፉ ሲሆን ቀደም ሲል በ2017 በጀት ዓመት መግቢያ ላይ በአምራች ኢንዱስትሪዎች የተነሱት ከኃይል አቅርቦት፣ ከኮንቴነር፣ ከትራንሰፖርትና ሎጀስቲክስ ጋር ተያይዞ የነበሩ ችግሮች እየተፈቱ ስለመሆኑ የተመዘገበው አፈፃጸም ማሳያ ነው ሲሉ ተሳታፊዎች ገልፀዋል ፡፡

ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የኤክስፖርት አቅም ለማሳደግ በኤክስፖርት አፈፃፀማቸው ከተመረጡ ስልሳ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር ከ2018 በጀት ዓመት ጀምሮ በወር ሁለት ጊዜ የኤክስፖርት አፈፃጸምን እንደሚገመግም ተገልጿል ፡፡

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post