አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በመጀመሪያ ሩብ ዓመት ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች 97.2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ተገኘ።

ጥቅምት 4/2018 ዓ.ም (ኢ.ሚ)ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጥሩ የኤክስፖርት አፈፃፀም ካላቸው አምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር የ2018 በጀት ዓመት የሩብ ዓመት ኤክስፖርት አፈፃጸም በተመለከተ የውይይት አካሄደ፡፡

የውይይት መርሀ ግብሩን የመሩት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል አምራች ኢንዱስትሪዎች ከመንግስት ማግኘት ያለባቸውን ድጋፍና ክትትል ለማግኘት ተዓማኒና ግልጽ መረጃ መስጠት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

አቶ መላኩ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በጥቅል ሲታይ በሩብ ዓመቱ ጥሩ የሚባል የኤክስፖርት አፈፃፀም ቢኖረውም እያንዳንዱ አምራች ኢንዱስትሪ በበጀት ዓመቱ ለማሳካት ያቀደውን ዕቅድ የማሳካት ሀገራዊ ተቋማዊ ግዴታ ያለበት መሆኑን ተገንዝቦ መስራት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሽ ለማ በሩብ ዓመቱ የኤክስፖርት አፈፃፀም ከሌሎች ጋር ሲነጻጸሩ ያነሰ አፈጻጸም ያሳዩ አንዳንድ ፋብሪካዎች የበለጠ ለመስራት መትጋት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊ አምራች ኢንዱስትሪዎች በበኩላቸው በ2018 በጀት ዓመት ከዘርፉ የመንግስት ሀላፊዎች ጋር በወር ሁለት ጊዜ በአካልና በበየነ መረብ(በዙም) እየተገናኙ መወያየት መጀመራቸው በርካታ ችግሮቻቸው እንዲፈቱ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡

በመርሀ ግብሩ ባለፉት ሶስት ወራት በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ኤክስፖርት በተደረሩጉ ምርቶች 97.2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን ና አፈፃፀሙም ከተያዘው ዕቅድ አኳያ 92% መድረሱን የዘርፉን የሩብ ዓመት ኤክስፖርት አፈፃጸም ሪፖርት ያቀረቡት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የወጭ ምርቶች ተወዳዳሪነት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘሪሁን አበበ ገልጸዋል፡፡

አፈፃፀሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ሩብ ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ45 በመቶ ማደጉን ያሳያል ብለዋል፡፡

Share this Post