6ኛው ዓለም አቀፍ የተቀነባበሩ የግብርና ምርቶች የንግድ ትርዒት በሚሊኒየም አዳራሽ ተከፈተ።

ግንቦት 8/2016(ኢ.ሚ) 6ኛው ዓለም አቀፍ የተቀነባበሩ የግብርና ምርቶች የንግድ ትርዒት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ተከፍቷል።

የንግድ ትርዒቱ ለተከታታይ ሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን 123 የሚሆኑ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ምርታቸውንና አገልግሎታቸውን እያስተዋወቁ ይገኛሉ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሃመድ ለኢዜአ እንደገለጹት ንግድና ትሪዒቱ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርታቸውን እንዲያስተዋውቁና በዘርፉ ኢንቨስትመንት ለመሳብ አላማ ያደረገ ነው።

የንግድ ትርዒቱ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎች የሚቀርቡበት፣ የገበያ ትስስር የሚፈጠርበት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ መልማት የሚችል ሀብትና ተስማሚ የአየር ሁኔታ እንዳላት ያስገንዘቡት ሚኒስትር ዴኤታው፥ የውጭ ባለሀብቶችም በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ የማስተዋወቅ ስራ በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በማሳደግ የተቀነባበሩ የግብርና ምርቶችን በሀገር ውስጥና በውጭ ገበያ በስፋት እንዲያቀርቡ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሌንሳ መኮንን በበኩላቸው የንግድ ትርዒቱ የቱሪዝምና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን የሚያነቃቃ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት በሀገር ውስጥና በውጭ በሚካሄዱ ኤግዚቢሽንና ባዛሮች በማስተዋወቅ ባለሀብቶችን እና ጎብኝዎችን ለመሳብ ጥረት እየደረገ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ነባር እና አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስፋትና በማስተዋወቅ የጎብኚዎችን ቆይታ ለማራዘም ስልት መቀየሳቸውን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የተርኪዬ አምሳደር በርክ ባራን የንግድ ትሪዒቱ የሀገራትን ንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ለማጠናከር ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በግብርና እና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረትም አድንቀዋል።

Share this Post