ሁለገብና ብሄራዊ የጥናትና ምርምር የቤተሙከራ ማዕከል እንዲቋቋም መስራት ይጠበቅብናል (ፕሮፌሰር ሽመልስ አድማሱ)

መጋቢት 15/2017 ዓ.ም (ኢሚ) የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን በጥናትና ምርምር የሚደግፉ ኢንስቲትዩቶች የነበሩ መሆኑን የጠቀሱት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በምግብ ምህንድስና ዘርፉ መሪ ተመራማሪና መምህር እንዲሁም በምግብ ደህንነት የተመሰከረለት የምግብ ደህንነት አዋቂው ፕሮፎሰር ሽመልስ አድማሱ አደረጃጀቶቹ በማዕከል የተዋቀሩ መሆኑን በማንሳት ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመተግበር የሚጠይቀው ፋይናንስ ከፍተኛ በመሆኑ ሁለገብና ብሄራዊ የጥናትና ምርምር የቤተሙከራ ማዕከል እንዲቋቋም መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ፖሊሲው ውስጥ የአምራች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት አቅምን ማሳደግ በሚል መጠቀሱ ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ቢሆንም ችግር ፈች የሆኑ ተግባራዊ ስራዎችን በስፋትና በጥራት ወደ መሬት በማውረድ የዘርፉን ሀገራዊ ተልዕኮ እውን ለማድረግ መስራት የሁሉም ተዋንያን ሚና መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።

አንድን ላም ዝርያዋን በጥናት ላይ ተመስርቶ ዝርያዋን በማሻሻል ሳይንሱ በሚጠይቀው ልክ እየተንከባቡ በመመገብ ወተት እንዲትሰጥ መጠበቅና በዘፈቀደ የምትያዝን ላም ተመሳሳይ የወተት ምርት እንድትሰጥ እንደማይጠበቅ ሁሉ በጥናትና ምርምር ስራዎች ያልተደገፈን ዘርፍ ተወዳዳሪና ምርታማ እንዲሆንና የተሻለ ሀገራዊ የእድገት አስተዋፅኦ እንዲያበረክት መጠበቅ የእልም ቅዠት ከመሆን በዘለለ ፋይዳ እንደማይኖረው ገልፀዋል ።

በጥናትና ምርምር ውጤቶች ቻይና ቀዳሚ አሜሪካ 2ኛ ደረጃ መሆናቸውን ያነሱት ፕሮፌሰሩ ሀገራችን 96ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ገልፀዋል።

ጥናትና ምርምር የአንድን ችግር ስረመሰረት በመረዳት መፍትሔ ለመስጠት ወሳኝ በመሆኑ የትኛውም ዘርፍ ለተግባራዊ ለጥናትና ምርምር ስራ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post