የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ኢንዱስትሪያላይዜሽን ለማምጣት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ ።
መስከረም 19/2018 ዓ.ም (ኢሚ) የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ከተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO) ኢትዮጵያ ተወካይ እና የአፍሪካ ህብረት እና የዩኔሲኤ(UNCA) ዳይሬክተር ስቴፋን ካርጋቦ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ውይይታቸውም ኢንዱስትሪያላይዜሽንን ለማምጣት እየተሰሩ ካሉ ስራዎች መካከል ሁለቱ ተቋማት በጋራ ሲሰሩባቸው በነበሩባቸው የጋራ አጋርነት ፕሮግራም (program for partnership) PCP) ፣በልህቀት ማዕከል ግንባታ፣ የሞጆ ሌዘር ሲቲ (ሞጆን ወደ ዘመናዊ፣ ስነ-ምህዳር ተስማሚ እና ተወዳዳሪ የቆዳ ማምረቻ ማዕከል ለማድረግ በቆዳ ኢንዱስትሪ ክላስተር እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ዳር የማድረስ) እና የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አቅም ግንባታና አስፈላጊ ድጋፎች ላይ ዋና ትኩረቱን አድርጓል፡
ኢንዱስትሪያላዜሽን ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ መሰረታዊ ጉዳይ ነው ያሉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል መንግስት ላለፉት አመታት በብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ እድገት አማራጮች ላይ ያተኮረ ሀገረ በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በማድረግ ውጤት ካመጣባቸው ዘርፎች መካከል የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጋራ አጋርነት ፕሮግራሞች ለጋራ ጥምረት እና ለፕሮጀክት ተግባራዊነትና አፈጻጸም ወሳኝነት እንዳለው የገለጹት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል የልህቀት ማዕከል ግንባታ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ትልቅ የልህቀት ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግል፣ የኢትዮጵያ ተቀናጀ አግሮ ኢንዱትሪ ፓርኮች ለአብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት በተምሳሌትነት የሚነሳ እንደሆነ አንዲሁም የሞጆ ሌዘር ሲቲ ግንባታ ጋር በተያያዘ ዘመናዊ፣ ስነ-ምህዳሩ ተስማሚ እና ተወዳዳሪ የቆዳ ማምረቻ ማዕከል መገንባት የሚያመጣውን አዎንታዊ አስተዋጽኦ በማንሳት በነዚህ ጉዳዮች ላይ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት እንደ ሀገር ኢንዱስትሪያላይዜሽን ለማምጣት በሚሰሩ ስራዎች ውስጥ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን ያቀረቡት አቶ መላኩ በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO) ኢትዮጵያ ተወካይ እና የአፍሪካ ህብረት እና የዩኔሲኤ(UNCA) ዳይሬክተር ስቴፋን ካርጋቦ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለበርካታ አፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት የሚሆን ተሞክሮዎች ያሏት ሀገር መሆኗን በማንሳት በቀጣይም እንደ ሀገር ኢንዱስትሪያላዜሽንን ለማምጣት በሚደረገው ርብብር እያደረጉ ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡