የአምራች ኢንዱስትሪ ማህበራት የአደረጃጀት መጠንከር ለዘርፉ ተልዕኮ ስኬት ቁልፍ ሚና አለው (ወ/ሮ ካሳየ ዋሴ)

መጋቢት 15/2017 ዓ.ም (ኢሚ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ታምርት ፕሮጀክት ለኢንዱስትሪ ማህበራት የቦርድ አመራሮች ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና እና ቶኒ ብሌር ኢንስቲትት ጋር በመተባበር የአገር ውስጥ የኢኮኖሚ ልማት አንቀሳቃሾች የኢንዱስትሪ ማህበራት ሚና፣ በአለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ላይ የኢንዱስትሪ ማህበራት ሚና እና የዘርፍ ማህበር አመራር እና አስተዳደር በሚሉ ሶስት ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ከ50 በላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተደራጁ የአምራች ኢንዱስትሪ ማህበራት አመራሮች ስልጠና መሰጠቱን ያስታወሱት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የብቃትና ፈቃድ አገልግሎት መሪ ሥራ አስፈፃሚና የኢትዮጵያ ታምርት የግሉ ዘርፍና የኢንቨስትመንት ክላስተር ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ካሳዬ ዋሴ የአምራች ኢንዱስትሪ ማህበራት የአደረጃጀት መጠንከር ለዘርፉ ተልዕኮ ስኬት ቁልፍ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ሀገራት በዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅት ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲሁም እንደ የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ባሉ ዓለም አቀፍ ፎረሞች ላይ አብዛኛውን ጊዜ አምራች ኢንዱስትሪዎቻቸውን እንደሚወክሉ የጠቀሱት ወ/ሮ ካሳየ የአምራች ኢንዱስትሪ ኩባንያ ባለቤቶች በእነዚህ መድረኮች ላይ በመሳተፍ ዘርፉን የሚጠቅሙ ፍትሃዊና ተወዳዳሪ ለሆነ ዓለም አቀፍ የገበያ ተደራሽነትና ተፈላጊነት አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ፖሊሲዎች ተዘጋጅተው ወደ ተግባር እንዲገቡ ከማድረጉም ባሻገር በየጊዜው ለሚዘጋጁ ፖሊሲዎችና የማስፈፀሚያ ስትራቴጅዎች የመነሻ ሀሳብ በማቅረብ የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥ የአሰራር ስርዓት እንዲዘረጋ በማድረግ አበርክቷቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ሀገር በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ቀውሶች በምትፈተንበት ጊዜ የአምራች ኢንዱስትሪ ማህበራት ለመንግስት ድጋፍ በመስጠት፣ ዓለም አቀፍ ምላሾችን በማስተባበር እንዲሁም ኢንዱስትሪዎች ለሚገጥሟቸው ፈተናዎች ጠንካራ ሆነው እንዲቀጥሉ የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራ በመስራት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱ ጠቁመዋል ፡፡

የዘላቂ ልማት አስፈላጊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ማህበራት የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ትርፋማነት የሚያሻሽሉ ስራዎችን ከመስራት ባለፈ የሚመረቱ ምርቶች ዓለማቀፋዊ መስፈርቶችን የሚያሟሉ፣ ተፈላጊነታቸው የጨመረ፣ የጥራት ደረጃቸው የላቀ እንዲሆኑና አረንጓዴ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለሥነ ምህዳር ምቹ የአመራረት ስርዓትን የተከተሉ በመሆን የሸማቹን ፍላጎት ያሟሉ እንዲሆኑ በማድረግ በአምራቹና በተጠቃሚው ማህበረሰብ መካከል እንደ ድልድይ ሆነው ማገልገል እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል፡፡

መሪ ስራ አስፈፃሚዋ አክለውም ጃፓን የግሉን ዘርፍ ያጠናከረችበትን ምርጥ ተመክሮ በጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ቡድን አማካኝነት የሀገራትን ልምድና ተሞክሮ ለአምራች ኢንዱስትሪ ማህበራት አመራሮች የማስረዳት ስራ መሠራቱን ተናግረዋል ፡፡

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post