የግብርና ትራንስፎርማሽንን ስናስብ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን መደገፍ ያስፈልጋል (ክቡር አቶ መላኩ አለበል)

ሚያዚያ 09/2016 ዓ.ም (ኢ.ሚ)የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ከተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የዘላቂ ልማት ግብቦች ፈጠራ እና ኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ዳይሬክቶሬት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ጉንተር በገር ከተመራ ልዑክ ቡድን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ በማተኮር ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ሀገር አቀፍ አጋርነት (PCP) ፕሮግራም አተገባበር፣ ዘላቂ የልማት አቅምን ማሳደግ ዓላማው ያደረገ የልህቀት ማዕከል ለማቋቋምና ሌሎች የጋራ ትብብር በሚያደርጉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

ሚኒስትሩ አቶ መላኩ የኢትዮጵያ መንግስት ከተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(UNIDO) ጋር የተተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፖርኮችን ውጤታማ በማድረግ የአርሶና አርብቶ አደሩን ኑሮ በማሻሻል የኢኮኖሚ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ሂደቱን ዕውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ተስፋ ሰጭ የትብብር ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አነስተኛ አርሶ አደሮች ጥራት ያለው በርካታ የግብርና ምርት በማምረትና ለኢንዱስትሪዎች በማቅረብ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማሳደግ አስተዋፅኦው የላቀ መሆኑን የገለፁት አቶ መላኩ የግብርና ትራንስፎርማሽንን ስናስብ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን መደገፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪያላይዜሽን ጉዞ ለማፋጠን የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ ወደ ተግባር ተገብቶ አበረታች ስኬቶች እየተመዘገቡ ነው ያሉት ሚኒስትሩ የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(UNIDO) እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ለንቅናቄው ዓላማ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የዘላቂ ልማት ግብቦች ፈጠራ እና ኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ዳይሬክቶሬት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ጉንተር በገር በበኩላቸው ለሀገር አቀፍ አጋርነት (PCP) ፕሮግራም አተገባበር፣ ዘላቂ የልማት አቅምን ማሳደግ ዓላማው ያደረገ የልህቀት ማዕከል ለማቋቋም የተደረሰው ስምምነት ፍሬ እንዲያፈራ ለማድረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰሩ ገልፀዋል ።

#ኢትዮጵያ_ታምርት #እኛም_እንሸምት

Share this Post