የኢትዮጵያን ምርቶች በአለም አቀፍ መድረኮች በማስተዋወቅ ረገድ የስፖርቱ ዘርፍ ትልቅ ሚና አለው (አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ)

ሚያዝያ 9/2016 ዓ.ም በተሰጠው መግለጫ የኢትዮጵያ ታምርት አገራዊ ንቅናቄ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) በይፋ የተጀመረበትን 3ኛ አመት አስመልክቶ ሀገር አቀፍ ኤክስፖ መዘጋጀቱን የጠቆሙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ዓላማውም የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግር በመቅረፍ በዘርፉ ዘላቂ ምርትና ምርታማነትን ማምጣት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የ2016ዓ.ም የንቅናቄውን ዝግጅት በተመለከተም ከተዘጋጁት መርሃ ግብሮች ውስጥ አንዱ የ10 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው ይህም በስፖርት ትጥቅ አምራችነት ለተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች የገበያ ትስስር በመፍጠር እና አዳዲስ አምራቾችን ወደ ዘርፉ እንደሰማሩ በማድረግ፣ ጤናማና በስፖርት የዳበረ አምራች ማህበረሰብ በመፍጠር፣ የሀገር ውስጥ ምርቶችን በማስተዋወቅና የመጠቀም ዝንባሌዎችን እንዲዳብር በማድረግ ረገድ ጉል ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያን ምርቶች በአለም አቀፍ መድረኮች በማስተዋወቅ ረገድ የስፖርቱ ዘርፍ ትልቅ ሚና ያለው በመሆኑ አምራች ኢንዱስትሪዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉም አቶ ታረቀኝ አክለዋል፡፡

መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ባደረገው ሩጫ ከዘጠኝ ሺ በላይ የአምራች ኢንዱስትሪ ተዋናዮች፣ ከአንድ ሺ በላይ ታዋቂ አትሌቶች እና 22 ክለቦች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች በግል ተወዳድረው ከ1ኛ እስከ 5ኛ ለሚወጡ የ250 ሺ ፣የ150ሺ ፣ የ100 ሺ፣ የ50 ሺ እና የ25 ሺ ብር እንዲሁም በሁለቱም ጾታ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ለሚወጡ የክለብ ተወዳዳሪዎች የ100 ሺ፣ የ75 ሺ እና የ50 ሺ ብር የብርና የሜዳሊያ ሽልማቶች እንደተዘጋጀ በመግለጫው ተብራርቷል፡፡

Share this Post